Fana: At a Speed of Life!

በወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ድንገት የተገናኙት ወንድም እና እህት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ተለያይተው ቆይተው ባልጠበቁትና ባልገመቱት ሁኔታ እህትና ወንድም ለእናት አገር ጥሪ ምላሽ ሰጥተው ለዘመቻ በከተቱበት አጋጣሚ ድንገት ሊገናኙ ችለዋል።

ወንድም ከአዲስ አበባ እህት ደግሞ ከደባርቅ መጥተው ብርሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መዕከል ውስጥ ድንገት ተገናኝተዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪው እሱባለው ማሞ፤ ቀደም ሲልም አገሩን በውትድርና የማገልገል ፍላጎት ስለነበረው ለአገር ህልውና የተደረገውን ጥሪ ተቀብሎ ብርሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ገብቷል።
እሱባለው አሁን ላይ ብርሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምልምል ወታደር ሆኖ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰደ ይገኛል።

ከእለታት አንድ ቀን በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ከስልጠና በኋላ (ፎሌን) የሰው ሃይል ቆጠራ ሲደረግ ‘የዓለምወርቅ ማሞ’ የሚል ስም ሲጠራ ይሰማል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የምትኖረውን የእህቱን ስም እንደሰማም “የስም መመሳሰል ሳይሆን አይቀርም” በማለት እያመነታ ‘ግን ለምን አላጣራም’ ማለት ጀመረ።

እሱባለው ጥርጣሬው እውነት ነው፤ እሱ ከአዲስ አበባ እህቱ ደግሞ ከደባርቅ ለአንዲት ኢትዮጵያ ዘማች ለመሆን ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተገናኙ።

”እህቴ ወደ ማሰልጠኛ ትገባለች ብዬ አልገመትኩም፤ የአገራችን ጉዳይ ከሁለት የተለያዩ ከተሞች ለአንድ አላማ አገናኝቶናል” ብሏል።

አገር እናትም አባትም በመሆኗ፤ አገር ከሌለ ማንም መኖር ስለማይችል አገርን መጠበቅ የሁሉም ግዴታ መሆኑን እሱባለው ይናገራል።

የእሱባለው ታናሽ እህት ምልምል ወታደር የዓለምርቅ ማሞ፤ ታላቅ ወንድሜን በማሰልጠኛው በማግኘቴ ደስ ብሎኛል ብላለች።

”ሰልጥኜ አገሬን ለመጠበቅ ነው የመጣሁት፤ እናት አባቶቻችን የሚኖሩት እኛ አገር ስንጠብቅ ነው፤ አገር ከሌለ ምንም የለም” ማለቷን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.