Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ላይ በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል ከ800 ቢሊየን እስከ 2 ትሪሊየን ይመዘበራል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በጄኔቫ የደህንነት ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪዎችና ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ለአራት ቀናት በሚሰጠው በዚህ ስልጠና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚሰሩ መርማሪዎች፣በክልሎች የሚገኝ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቅርንጫፍ የወንጀል መርማሪዎችና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

ስልጠናው በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል ላይ ያተኮረ ሲሆን በጄኔቫ የደህንነት ዘርፍ አስተዳደር ማዕል እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ስልጠናውን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ወንጀለኞች የተለያዩ የአፈጻጸም ዘዴ በመጠቀም በህገ-ወጥ ተግባር የተገኘውን ገንዘብና ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ በርካታ የህዝብንና የመንግስት ሀብት በመበዝበዝ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ መሆናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ዓመት ብቻ ከዓለማችን አጠቃላይ ዓመታዊ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ከ2 እስከ 5 በመቶ ወይም ከ800 ቢሊየን እስከ 2 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር በዚህ ወንጀል እንደሚመዘበር የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ ዕፅዋትና የወንጀል ቁጥጥር ቢሮ ያደረገው ጥናት ያመለክታል ብለዋል አቶ ሙሊሳ ።

በኢትዮጵያም የችግሩ መጠን ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሙሊሳ  የወንጀል ቡድኖቹ በአደገኛ ዕፅ ዝውውር፣በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣በሙስና እና ብልሹ አሰራሮች፣በዕገታ፣በህገ-ወጥ ማዕድን ዝውውር፣በዝርፊያ እና በመሳሰሉት የወንጀል ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ ህገ-ወጥ ገንዘቡን እንደሚሰበስቡ በመግለጽ ወንጀሉ እየተስፋፋ ከመሄዱ በፊት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ በአጭሩ መግታት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሰልጣኞቹ ከስልጠናው የሚያገኙትን ልምድ በቀጣይ ለሚያከናውኑት የህግ ማስከበር እና የምርመራ ሥራቸው መጠቀም እንዳለባቸውም የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አሳስበዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.