Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ምርታማነትን ማሳደግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ምርታማነትን ማሳደግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተገለፀ።

ይህ የተገለጸው “ሀገራዊ አምራችነት ” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአዲስ ወግ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው።

በውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ታምራት ኃይሌ፥ በዓለም ታሪክ የሀገራት መስተጋብር እየተጠናከረ በመጣ ቁጥር ውድድሩም ፈታኝ እየሆነ ነው ብለዋል።

በትስስሩ ምክንያት በአንደኛው የዓለም ክፍል የሚፈጠር ችግር በሁሉም ቦታ ተጽዕኖው እየጎላ መምጣቱንም አንስተዋል ።

ይህንን ፈታኝ ክስተት ለመሻገር ለሀገራት ምርታመነት እና ተወዳዳሪነት የግድ ብሏል ነው ያሉት።

ሌላኛው ሀሳብ አቅራቢ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በበኩላቸው÷ አሁን ላይ  በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ለውጥ በድሮ የልቦና ውቅር መሻገር አንችልም ብለዋል።

እንደሳቸው ገለጻ በቀደመው የምርታማነት ሕግ ጥራት ሲባል ረዘም ያለ ጊዜ እና ከፍተኛ  ዋጋን  የሚጠይቅ ነበር። አሁን ግን የውድድር ሕጉ መቀየሩን ነው ያስረዱት።

በአሁናዊው የምርታማነት ሕግ ጥራት ማለት ብክነትን በመቀነስ በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ዋጋ የደንበኛን ፍላጎት ማርካት እንደሆነ ገልጸዋል ።

ከዚህ አንጻር ሲታይ በኢትዮጵያ ያለው ምርታማነት ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነ ምሁራኑ አንስተዋል።

በአዲስ ወግ ተወያዮች እንዳነሱት፥ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ያለው ምርታማነት በአማካይ ከ50 በመቶ ያነሰ ነው።

ይህ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ካለው ምርታማነት አንጻር ሲታይ እንኳ ዝቅተኛው ነው።

ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ይፋ የተደረገው ” ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ” ጥሩ መፍትሔ ነው ብለዋል።

የመፍትሔ ሀሳቦችን ያመላከቱት ተወያዮቹ አምራችነትን ለማሳደግ መንግስት ለኢንዱስትሪዎች የሚያደርገው ድጋፍ ጥራት እና ውጤታማነት ላይ መመስረት አለበትም ብለዋል።

አምራችነት የብዙ ስራዎች ድምር ውጤት በመሆኑ እንደ ሀገር ለሰው ኃይል፣ ለጊዜ እና እያንዳንዱን አቅም መጠቀም ላይ ያለንን ዕይታ መቀየር አለብንም ነው ያሉት ።

አምራችነት በኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሀገራዊ ዕድሎችን በተገቢው መንገድ አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል ።

አሁን አደጉ የሚባሉ ሀገራት በሙሉ የደረሱበት ደረጃ መሰረቱ የትናንት የማይታይ ሀሳብ በመሆኑ÷ ዛሬም ኢትዮጵያውያን የልቦና ውቅር ለውጥ በማምጣት የተሻለ ነገ መፍጠር ትችላለች ብለዋል።

በዚህ ሂደት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለውን አቅም በመጠቀም በየተሰማራንበት መስክ መትጋት አለበትም ተብሏል ።

በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.