Fana: At a Speed of Life!

በዓለም አቀፍ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በዓለም አቀፍ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን በዛሬው እለት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ መነሻቸውን ብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ በማድረግ ወደ ተለያዩ ሃገራት ለመድረስ ጉዞ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግስተአብ በየነ ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦቹ ዕፁን በውስጣዊና ውጫዊ የሻንጣ አካል በመደበቅ፣ በመዋጥ እንዲሁም የጡት መያዣና የተለያዩ የማዘዋወሪያ ዘዴዎችን ተጠቅመው ለማሳለፍ ሙከራ ማድረጋቸውንም ኮማንደር መንግስተአብ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት 13 ናይጄሪያውያንና አንዲት ብራዚላዊትን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ተጠርጣሪዎቹ ከ14 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን ይዘው የተገኙ ሲሆን አደገኛ ዕፁ በደቡብ አሜሪካ አካባቢ የሚመረትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘዋወር መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት ወደ 24 የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 39 ኪሎ ግራም ኮኬይንና 36 ኪሎ ግራም ካናቢስ መያዙንም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.