Fana: At a Speed of Life!

በዘላቂ የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምስት ክልሎች በተመደበ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ በተካሄደው ዘላቂ የኑሮ ዋስትናን ማረጋገጥ ፕሮግራም 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በፕሮግራሙ የተከናወኑ ስራዎችን ለመገምገም የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የፕሮግራሙ ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ተፈራ እንደተናገሩት፤ ከኔዘርላንድስ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሙ በትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልልች የምግብ ዋስትና እጥረት ባለባቸው 62 ወረዳዎች ውስጥ የተካሄደ ነው።

በወረዳዎቹ በዓመት እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ የምግብ እጥረት ያለባቸው ቤተሰቦች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ያመላከቱት አስተባባሪው ይህንን ችግር ለማቃለል ፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በክልሎቹ ከሚገኙ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ግብርና ቢሮ፣ የአደጋ ስጋት መከላከልና ስራ አመራር ኮሚሽንና ምርምር ተቋማት ጋር በአጋርነት መሰራቱንም ገልጸዋል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በፕሮግራሙ አማካኝነት የምግብ እጥረት ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ምርጥ የግብርና ተሞክሮዎች የመለየት፣ የማላመድና የማስፋት ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ የተሻሻሉ የሰብል፣ ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ እና የስራስር ዘሮችን ለምግብ ዕጥረት ተጋላጭ ለሆኑ አርሶ አደሮች በማሰራጨት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

እንዲሁም በአነስተኛ ማሳ ላይ ምርምር በማካሄድ ምርታማነትንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት ስራ ተከናውኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.