Fana: At a Speed of Life!

በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ኢንዱስሪ ፓርክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከማህበራት ጋር ትስስር መፍጠራቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ኢንዱስሪ ፓርክ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ተባለ፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚጠቀምባቸው ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ግብዓቶች የሀገር ውስጥ ምርችን የሚጠቀም በመሆኑ የእሴት ጭማሪ እና የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ፓርኩ በመጀመርያ ምዕራፍ 300 ሄክታር ላይ እየለማ የሚገኝ ሲሆን የገጠር ማዕከላቱ እያንዳንዱ በ10 ሄክታር ላይ እየለሙ ሲሆን ፓርኩ የምግብ ምርቶች ማምረቻ ኢንዱስሪዎች ሊያሟላቸው የሚገቡ መሰረተ ልማቶች እና የግንባታ ደረጃዎች በተሟላ መልኩ በመከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩ 11 የማምረቻ ሼዶችን ለሙከራ ማሳያነት የገነባ ሲሆን ፓርኩ ለባለሀብቶች ሁለት አማራጮችን በማስቀመጥ የተገነቡ ማምረቻ ህንፃዎችን ማከራየት እና የለማ መሬትን በማስተላለፍ አምራቾች የራሳቸውን የማምረቻ ሼድ እዲገነቡ በማድረግ የሚያስፈልጉ የመንገድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ፓርኩ በመገንባት ላይ ነው፡፡

በፓርኩ ውስጥ ሰንቫዶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር የተባለ የኔዘርላንድ ባለሀብቶች ንብረት የሆነ የአቮካዶ ዘይት አምራች እና ዶሊ ፉድ ፕሮሰሲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ወተት የሚያቀነባብር የቻይናውያን ባለሀብቶች ንብረት የሆነ ድርጅት ስራ ጀምረዋል፡፡

በተጨማሪም አንድ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ማርን የማቀነባበር ስራ በፓርኩ ውስጥ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ሰንቫዶ ማኑፋክቸሪንግ ለምርት ግብአትነት የሚጠቀምበትን የአቮካዶ ምርት ለማግኘት ከህብረት ስራ ማህበራት ከተውጣጡ 78 ሺህ ገበሬዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በአሁኑ ወቅት በቀን 52 ቶን አቮካዶ እየሰበሰብ ዘይት በማምረት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀን 12 ሺህ ሊትር ወተት የማቀነባበር አቅም ያለው ዶሊ ፉድ ፕሮሰሲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ይህንን ግብአት ለማግኘት ከአስራ ሁለት ሺህ በላይ ገበሬዎች ተለይተው ከአምስት ሺህ ገበሬዎች ጋር በመተሳሰር ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

ፓርኩ ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር አረንጓዴ ልማት እና የፓርክ ማስዋብ ስራዎች በአከባቢው ወጣቶች ከማስራት በተጨማሪ በአከባቢው ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር አከባቢው ባሉት እምቅ አቅሞች ላይ ጥልቅ ጥናት እና ባለሀብቶችን የማማከር ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪ ለአከባቢው ነዋሪዎች ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በባለሀብቶቹ ተሳትፎ አዳሪ ትምህርት ቤት ያቋቋመ ሲሆን ለነዋሪዎችም ንፁህ የመጠጥ ውሀ በማቅረብ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.