Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በ147 ሚሊየን ብር በጀት 7 አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በደቡብ ክልል በ147 ሚሊየን ብር በጀት 7 አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውል ስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ እንደገለጸው በክልሉ ከ2009 ጀምሮ በተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም በ2 ምዕራፎች የመስኖ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል።

በቢሮው የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ምራ ሙሃመድ እንዳሉት በመጀመሪያው ምዕራፍ 10 አነስተኛ መስኖዎችን ለመገንባት ታቅዶ 9 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን አንድ ፕሮጀክት በቅርብ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ቢሮው በ2ኛው ምዕራፍም የ11 አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማካሄድ እየሰራ እንደሆነ ያነሱት አቶ ምራ ከእነዚህ ውስጥ የ7ቱ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በቀጣዮቹ 15 ቀናት ውስጥ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

ሰባቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች በጉራጌ ዞን ማረቆ ፣በከንባታ ጠንባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ፣በጋሞ ዞን ከምባ ፣በጎፋ ዞን ዑባ ደብረ ጸሃይ ፣በዳውሮ ዞን ሎማ፣በሀዲያ ዞን ሶሮና በጌዴኦ ዞን ኮቸሬ ወረዳዎች የሚገነቡ ናቸው።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ147 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን÷ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ 525 ሄክታር መሬትን በማልማት 2ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም አላቸው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስትር አስተባባሪና የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የመስኖ ልማት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው በክልሉ የመካከለኛና አነስተኛ መስኖ ተቋማትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

በክልሉ ከፍተኛ የመስኖ አቅም ቢኖርም የለማውም ሆነ ከዘርፉ የሚገኘው ሀብት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።

የሰባቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ተጠናቆ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደርጉ ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

አቶ ምራ እንዳሉት ደግሞ ፕሮጀክቶቹ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ሲሆን በአካባቢዎቹ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ፣ገበያ ተኮር የመስኖ ልማት፣የመስኖ ውሃ ተጠቃሚ ማህበራትን የማጠናከር ስራዎች በተቀናጀ መንገድ ይሰራሉ።

ግንባታቸው በደቡብ ውሃ ስራዎች ድርጅት አማካኝነት የሚካሄድ እንደሆነም ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.