Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በ2012 በጀት አመት 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2012 በጀት አመት ከ9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ዳያስፖራዎች በግልና በአክሲዮን ፈቃድ መሰጠቱን የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው በክልሉ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ የኢንቨስትመንት ፍሰቱም እድገት እያሳየ መምጣቱን ነው ያስታወቀው፡፡

በዚህም በክልሉ መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ 454 በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ የልማት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል ተብሏል፡፡

በተለይም ደግሞ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በግብርና፣በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች በስራ እድል ፈጠራም ሆነ በወጪ ንግድ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አስራት አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አስራት አሰፋ በ2012 በጀት አመት የተሰጠው ፈቃድ ከ2011 በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ6 ቢሊየን ብር ካፒታል ብልጫ አለው ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ የክልሉ መንግስት ምላሽ ያላገኙ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በመለየት ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረጉ እና የክልሉን እምቅ ሀብቶች በማስተዋወቅና የዳያስፖራውን ህብረተሰብ ተሳትፎ በማጠናከርና የተሻለ የመሬት አቅርቦትን በማመቻቸት ረገድ የሰራቸው ውጤታማ ስራዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ከ53 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸውም ኮሚሽነሩ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ 71 በግብርና፣ 200 በአገልግሎትና 183 ደግሞ በኢንዱስትሪ ዘርፎች ፈቃድ የወሰዱ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.