Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የምርጥ ዘር ፍላጎትን ለማሟላት ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅትም በደቡብ ክልል ለበልግም ሆነ ለመኸር እርሻ የምርጥ ዘር አቅርቦቱ ደረጃውን የጠበቀና በመጠንና በአይነት ያለውን ፍላጎት የሚያሟላ እንዲሆን ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

በተጨማሪም እንደየ ስነ ምህዳሩ ተስማሚና ውጤታማ የሆኑ ዘሮችን የማቅረቡ ስራ ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ አለበት ተብሏል።

የምርጥ ዘር ብዜት ተግባርና ግብይት ከገቢ ምንጭነት፣ ከምግብ ዋስትና መረጋገጥና ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተቆራኝቶ ሊታይ እንደሚገባውም ተጠቁሟል።

የበልግና የመኸር ወቅት የምርጥ ዘር ፍላጎትን ለማሟላት ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

እንደ ሀገርም ሆነ በደቡብ ክልል የግብርና ምርትና ምርታማነት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም እስከ አሁንም ድረስ የእድገት ሁኔታው ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ለችግሩም የምርጥ ዘር አቅርቦት ደካማ መሆን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ግብርና ዘርፍ አስተባባሪና የቢሮው ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ተናግረዋል ።

አርሶ አደሩ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣ ዘንድ ማዳበሪያን በተገቢው መንገድ ከመጠቀምና የተሻሻሉ አሰራሮችን ከመተግበር ባሻገር ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር ወቅቱን ጠብቆ በፍላጎቱ ልክ ማግኘት እንዳለበትም አቶ አንተነህ ገልጸዋል ።

ሆኖም በአይነትም ሆነ በመጠን በአርሶ አደሩ ፍላጎት መጠን ምርጥ ዘር እየቀረበ አይደለም ያሉት የቢሮ ሃላፊው ለችግሩ የመሬት አቅርቦት ክፍተትና ቅንጅታዊ አሰራር አለመዳበር አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት የምርጥ ዘር ብዜት ስራ በሞዴል አርሶ አደሮች፣በድርጅቶችና በመንግስት ደረጃ እየተካሄደ ቢሆንም የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

ክፍተቱን ለመሙላትም የዘር ብዜትን የማጠናከር፣ዘርፉን የማስተዋወቅ እና የማህበራትና የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ የማጎልበት ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል ።

በመድረኩ ላይ በምርጥ ዘር ብዜት ስራ የተሰማሩ ድርጅቶችና ማህበራት ፣በሰብል ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ፣የምርምር ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዪኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.