Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ አይደለም – የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እየተተገበሩ አለመሆኑን የደቡብ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ገለጹ።
በክልሉ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቅ በኋላ የጤና ሚኒስቴር ያወጣቸው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መመሪያዎች በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል።
የህብረተሰቡን መዘናጋት ለመቅረፍም በክልሉ “ማስክ ሳያደርጉ አገልግሎት አልሰጥም” የተሰኘ አዲስ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ንቅናቄ መጀመሩን ነው የገለጹት።
ይህን ንቅናቄ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ማስጀመራቸውንም ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ዜጎች ቫይረሱ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ አቅም ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ቢገነዘቡም መመሪያዎችን ከመተግበር አንፃር ግን ከፍተኛ መዘናጋት ይስተዋልባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የህብረተሰቡን መዘናጋት ተከትሎም ቫይረሱ በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ÷ እስካሁንም ከ4 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ መረጋገጡንም ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ ያለው አጠቃላይ የቫይረሱ ምጣኔም 3 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ችግሩን ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ፡፡
በዚህ መሰረት ማንኛውም ዜጋ ወደ መንግስታዊም ሆነ የግል ተቋማት እንዲሁም ሰው በብዛት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሲሄድ ማስክ የማድረግ ግዴታ እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
አያይዘውም ገናን ጨምሮ በቀጣይ በሚከበሩ በዓላት ወቅት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ዜጎች የመከላከያ መንገዶችን በትክክል እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ከአርባምንጭ እና ወላይታ ሶዶ ባሻገር በተለያዩ የደቡብ ክልል ከተሞች ባደረገው ቅኝት ዜጎች በትራንስፖርት፣ በሆቴሎች እና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ላይ ኮሮናን ለመከላከል የሚያደርጉት ጥንቃቄ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተተወ ጉዳይ መሆኑን ታዝቧል።
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.