Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል 13 ከተሞች የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል 13 ከተሞች የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሊጀመር መሆኑን የደቡብ ክልል ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ፕሮግራሙን በማስመልከት የፌደራል ከተሞች ስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሀዋሳ ስልጠና ሰጥቷል።

ፕሮግራሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በ13 የተመረጡ ከተሞች እንደሚጀመር የገለጸው ቢሮው የፕሮግራሙ ዋና አላማም የከተማውን ነዋሪ ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ እንደሆነ ጠቁሟል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ የየአካባቢውን ውስን ሀብት፣ የህዝቡን እውቀትና ጉልበት በማቀናጀት የከተማውን ህዝብ የምግብ ዋስትና ችግር መቅረፍ የወቅቱ ቁልፍ ጥያቄ መሆኑን አንስተው፤ ለፕሮግራሙ ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።

በክልሉ ይህን የህዝብ ችግር ለመቅረፍ ራሱን የቻለ ኤጀንሲና በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የከተማ ምግብ ዋስትና እና የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት መቋቋሙን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትና እና ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ቡልቻ እንዳሉት፤ የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ በዚህ አመት ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በ13ቱ ከተሞች ይተገበራል።

በፌደራል ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ሰይፉ ለፕሮግራሙ ስኬት ህዝቡና የአመራር አካላት ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.