Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የምግብ እርዳታ ይሻሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዝናብ መቆራረጥ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በደቡብ ክልል 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የምግብ ድጋፍ እንደሚፈልጉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ያጋጠመው የአየር ንብረት ለውጥ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት የተመለከተ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ በተለይም በ2013 ዓ.ም ከበልግ ወቅት ጀምሮ የተከሰተው የዝናብ መቆራረጥ እና የአየር ንብረት መዛባት አርሶ እና አርብቶ አደሩን ለከፋ ጉዳት ዳርጓል፡፡

በዚሁ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የሰብል ውድመት መድረሱን እና 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።

ከእነዚህም መካከል 2 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የማካካሻ ዘር፣ የመኖና መድሃኒት አቅርቦት ሥራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሃለፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በ2014 ዓ.ም ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 66 ሺ 335 ህፃናት ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ችግር እንደተዳረጉ መገለጹንም ደሬቴድ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.