Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኮሪያ በአንድ ቀን 594 አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ኮሪያ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ።

የሃገሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንዳስታወቀው፥ በአንድ ቀን ብቻ 594 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል።

ይህም እስካሁን በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር 2 ሺህ 931 አድርሶታልም ነው ያለው።

አሁን ላይ በሃገሪቱ ያለው የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱንም ማዕከሉ ገልጿል።

አብዛኛው የቫይረሱ ተጠቂዎችም ከደቡባዊቷ ዳኤጉ ከተማ መሆናቸው ተገልጿል።

የሃገሪቱ ባለስልጣናትም ቫይረሱ “ከአምልኮ ስፍራ የቫይረሱ ተጠቂ በሆኑ አማኞች” አማካኝነት ሳይዛመት እንዳልቀረ ገልጸዋል።

በተያያዘም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ እና ኦሪገን ግዛቶች ሶስት አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል ተብሏል።

ግለሰቦቹ ቫይረሱ ታይቶባቸዋል ወደ ተባሉ አካባቢዎች፥ የተመዘገበ የጉዞ ሪፖርት የሌላቸው መሆኑም ነው የተገለጸው።

የዓለም ጤና ድርጅትን ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ደግሞ በአሜሪካ 59 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ያመላክታሉ።

መነሻውን ውሃን ከተማ ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ ከ50 በላይ ሃገራትን ሲያዳርስ፥ ከ83 ሺህ 650 በላይ ሰዎች ደግሞ አጥቅቷል፤ በትናንትናው እለት ብቻም ተጨማሪ ስድስት ሃገራትን አዳርሷል።

በቫይረሱ ሳቢያም ዓለም አቀፉ የአክሲዮን ገበያ አሽቆልቁሏል።

የዓለም ጤና ድርጅትም የቫይረሱ ስርጭት ዓለም ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል።

ድርጅቱ ቫይረሱ እንዲሰራጭ የሚያደርጉትን አጋጣሚዎች መቀነስና በአግባቡ መቆጣጠር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.