Fana: At a Speed of Life!

በዳያስፖራ ኤጀንሲ የተመራ የልዑካን ቡድን በዱባይና ሰሜን ኤመሬቶች ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የተመራ የልዑካን ቡድን በዱባይና ሰሜን ኤመሬቶች ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያየ።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የኤጀንሲው የልዑካን ቡድን በዱባይና ሰሜን ኤመሬቶች ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራትና አደረጃጀት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ተወያየ፡፡

በወቅቱም በዱባይና ሰሜን ኤመሬቶች የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄነራል አምባሳደር እየሩሳሌም አምደማርያም ዳያስፖራው ለሃገራዊ ጥሪዎች እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው ጊዜው የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው፣ በዱባይ አካባቢ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትም ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሃገራዊ ራዕይ መሳካት በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ሃገራዊ ጥሪዎች ዳያስፖራው እየሰጠ ስላለው ፈጣን ምላሽም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ተሳታፊዎች መንግስት ተገዶ ወደ ህግ ማስከበር ስራ እንዲገባ መደረጉና የተወሰደው እርምጃ የዘገየ ካልሆነ በቀር ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

ዳያስፖራው ባካበተው ዕውቀትና ልምድ ሃገሩን ለማገዝ ዝግጁነት እንዳለው፣ ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በጋራ ለማሰባሰብ እየተሰራ እንደሆነ፣ ከልዩነት ይልቅ ሃገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው፣ ዜጎች ወደ ዱባይና ሰሜን ኤመሬቶች በህጋዊ መንገድ ሄደው መስራት እንዲችሉ የተጀመሩ አሰራሮች በፍጥነት ወደ ተግባር ባለመግባታቸው የተፈጠረውን ህጋዊ ያልሆነ አካሄድ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ካደረጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በሰሜኑ የሃገራችን አካባቢ ለተጎዱ ሰዎች ማቋቋሚያ የሚሆን የ50 ሺህ ድርሃም ለመለገስ ቃል መግባታቸው እንዲሁም ዳያስፖራው የሃገሩን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

የልዑካን ቡድኑ ወደ አቡዳቢ በማቅናት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በከተማው ከሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር እንደሚወያይ ታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.