Fana: At a Speed of Life!

በድጎማ የሚቀርቡ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ የግል ባለሃብቶችን ለማሰማራት እየተሰራ ነው- የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በድጎማ የሚቀርቡ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ በዘርፉ የግል ባለሃብቶች በስፋት እንዲሰማሩ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ  የንግድ ውድድር እና ሸማቶች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ ቃዶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ስኳር፣ ዘይት፣ ስንዴ እና የመሳሳሉ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በየወሩ 10 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለተጠቃሚዎች እየቀረበ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፤ ስኳርም በ61 ዩኒየኖች እና በአንድ ፌደሬሽን አማካኝነት እየተሰራጨ መሆኑን አንስተዋል።

ይሁን እንጅ በሀገሪቱ በተፈጠረው የምዛንሬ እጥረት እና በክረምት ወቅት የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ምርት በማቆማቸው ምክንያት በስኳር ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ መደረጉን ነው የጠቆሙት።

ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሚሊየን ኩንታል ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ያነሱት አቶ አብዱለላዚዝ፥ በወቅቱ በገባው የስኳር ምርት ላይም በኩንታል 575 ብር ጭማሪ መደረጉን አብራርተዋል።

ይህን ተከትሎም በአንዳንድ ዞኖች ላይ በተዛባ መረጃ ምክንያት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉንም  ነው ሃላፊው ያብራሩት።

የስንዴ አቅርቦትን በተመለከትም መንግስት በስርጭት ሂደቱ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት እያካሄድ በመሆኑ ላላፉት አራት ወራት መቋረጡን ነው የጠቆሙት።

ምርቶች በተቆረጠላቸው ዋጋ እና ጊዜ ለተጠቃሚች ተደራሽ እንዲሆኑም አዳዲስ መመሪያዎችን በማውጣት እስከ ወረዳ ድረስ በተቋቋመው ኮሚቴ አስፈላጊ የቁጥጥር ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡም በህገ ወጥ ነጋዴዎች ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረግ መሰል ምርቶችን በህጋዊ መንገድ ከሚያቀርቡ የሸማች ማህበራት እንዲገዛ አሳስበዋል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.