Fana: At a Speed of Life!

በጅማ አዌቱ ወንዝ ዳርቻን ለማልማት የ600 ሚሊየን ብር የውል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጅማ ከተማን ለሁለት አቋርጦ የሚያልፈው የአዌቱ ወንዝ ዳርቻን ለማልማት የ600 ሚሊየን ብር የውል ስምምነት ተፈረመ።

የወንዝ ዳር ልማቱን በሚያከናውኑ በሳኢ መሀመድ፣ ሙስጠፋ ጀማልና ጥላሁን አበበ በተባሉ ሶስት የግንባታ ተቋራጮች የስራው ባለቤት ከሆነው የጅማ ከተማ አስተዳደር ጋር የውል ስምምነቱን ተፈርሟል።

የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ከድር ሀሰን የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ስራ በሶስት ስራ ተቋራጮች የሚገነባ ነው ብለዋል።

የወንዝ ዳርጃ ልማት ፕሮጀክቱ በከተማው አስተዳደር በሚመደብ በጀትና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በሶስት የሥራ ደረጃዎች ተከፋፍሎ የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።

የመጀመሪያው የፕሮጀክት ስራ በ101 ሚሊየን ብር በጀት የሚከናወንና በአስራ አንድ ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ቀሪዎቹ ሁለት ፕሮጀክቶች ደግሞ በ499 ሚሊየን ብር በጀት በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚከናወኑ የገለጹት ስራ አስኪያጁ አጠቃላይ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱ በሶስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ፕሮጀክት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የአዌቱ የህዝብ መናፈሻን ከትንሿ ስታዲየም የሚያገናኝ ድልድይ እንዲሁም የወጣቶች ማዕከል ግንባታ ያካለለ ልማት እንደሚካሄድ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የውሃ ማጣሪያ፣ የተለያዩ ድልድዮች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ቤተ መፅሐፍት፣ የወጣቶች መዝናኛዎችና የተለያዩ የገበያ ማዕከሎችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.