Fana: At a Speed of Life!

በጉራጌ ዞን ሲሊካ የተሰኘ ማዕድን ማውጫን በ550 ሚሊየን ብር ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከ550 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሲሊካ የተሰኘ ማዕድን ከአሽዋ በማውጣት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለሀገር ውሰጥ እና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ማውጫን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ የሚገነባው ይህ የማእድን ማውጫ 200 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ለተለያዩ የፋብሪካ ግብዓቶች የሚውል የ “ሲሊካ” ማዕድን ምርት ከአሸዋ ውስጥ በማጣራት እንደሚያመርት የኩባንያው ባለቤት አቶ ዳዊት ሽብሩ ተናግረዋል።

ኘሮጀክቱ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ምርቱን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ያቀርባል ተብሏል።

ፕሮጀክቱን ለመጀመር በተለያዩ የሥነ ምድር ባለሙያዎች ጥናት ሲደረግ እንደቆየም ተመላክቷል፡፡

በሥነ ስርዓቱ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ፥ “የብዙ ፀጋዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ጠላቶቻችን በሚሰጡን አጀንዳዎች ፀጋዎቿን ሳትጠቀምበት ቆይታለች” ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል በዓለም እጅግ ውድ የተባሉ የማዕድን ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፥ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሐብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፥ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገር ደረጃ የሚፈለገውን የ”ሲሊካ” ምርት ከማዕድን ዘርፉ ባለፈ ለግብርና፣ ለግንባታ፣ ለፋብሪካ የሚውል በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋልም ተብሏል።

“ሲሊካ ሳንድ” ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚያገለግል ሲሆን በተለይም ለብርጭቆ እና ለጠርሙስ፣ ለፅዳት ዕቃዎች፣ ለውሃ ማጣሪያ እና ማከሚያ፣ ለቀለም ፋብሪካ፣ ለብረታ ብረት እና አልሙኒየም ሥራ ፣ ለዘይት እና ጋዝ አምራቾች እንዲሁም ለተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንደ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።

በምንይችል እዘዘው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.