Fana: At a Speed of Life!

በጉራፈርዳ በህወሓት የጥፋት ሃይሎች በተሰጠ ተልዕኮ የ61 ዜጎችን ህይወት አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ወንድማማቾች ላይ ከሞት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት ተወሰነባቸው 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሚዛን ቦንጋ 4ኛ ተዘዋዋሪ ችሎት በጉራፈርዳ በህወሓት የጥፋት ሃይሎች በተሰጠ ተልዕኮ የ61 ዜጎችን ህይወት አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ወንድማማቾች ላይ ከሞት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት ወሰነባቸው፡፡
ቅጣቱ የተወሰነባቸው በጉራፈርዳ በህወሓት የጥፋት ሃይሎች በተሰጠ ተልዕኮ 12 ፌደራል ፖሊሶችን ፣4 የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እና ቀሪ ንፁሃን ዜጎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የ61 ዜጎችን ሕይወት አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ወንድማማቾች ላይ ነው፡፡
ከሞት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት የተቀጡት ግለሰቦች 1ኛ ከይሳ ይርጉ ፣2ኛ ጌች ይርጉ ፣ 3ኛ ሸርነክ ይርጉ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የደቡብ ክልል ዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ከመስከረም ወር 2007 እስከ 2009 ዓ.ም በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ስድስት ቀበሌዎች የሚኖሩ የአማራ ከልል ተወላጆችን ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን መሬታችሁ ተወሯል በሚል ግጭት እንዲነሳ ማድረጋቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህ ግጭት መነሻ በማድረግ በአካባቢው የነበሩ የአማራ ተወላጆችን በመግደል እንዲፈናቀሉና ቤታቸው እንዲቃጠል ከማድረጋቸው በተጨማሪ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ አስከባሪዎችን 12 የፌደራል ፖሊስ እና አራት መከላከያ አባላት ላይም የግድያ ወንጀል መፈጸማቸው ተጠቅሷል።
በሰባት ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾቹ የጦር መሳሪያ ይዞ ማመጽ ፤የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት ወንጀል በቀረበባቸው ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ 1ኛ ከይሳ ይርጉ በሞት እንዲቀጣ ሲወስን ÷2ኛ ጌች ይርጉ የ25 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ሸርነክ ይርጉ ደግሞ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.