Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል በሽብር ሴራ የተጠረጠሩ 65 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በጋምቤላ ክልል ከጽንፈኛው ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 65 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ህዝብ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የጽንፈኛው ቡድንና የሌሎች ቅጥረኞችን ሴራ በማምከን ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በክልሉ ህዝብና ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲያሴሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

የህወሐትና ከሌሎች የሽብር ቡድኖችን ጋር በመቀናጀት ቅጥረኞችን በማሰማራት በንጹሃን ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ አቅዶ ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የፖሊስ ኮሚሽኑ የጥፋት ቡድኑን ሴራ በመገንዘብ ከሌሎች የፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል እስከ ትናንት ባለው ጊዜ 65 ተጠርጣሪዎችን በህግ በቁጥጥር ስር ማዋሉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በጋምቤለ ከተማና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የብሔር ግጭት በማስነሳት በሰው ህይወትና በተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ በመንቀሳቀስ በመጠርጠራቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

የጽንፈኛው ህወሓት ቡደን ካፈነገጠበት ጊዜ ጀምሮ በጸጥታ አካላትና በክልሉ የፖለቲካ አመራር ጭምር በተከናወኑት ስራዎች የክልሉ ሰላም ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ሁኔታ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.