Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል በኑዌር ዞን ሁለት ወረዳዎችን ከዞኑ ከተማ ጋር ለማገናኘት የተሰራው ድልድይ ለትራፊክ ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በኑዌር ዞን ሁለት ወረዳዎችን ከዞኑ ከተማ ጋር ለማገናኘት በባሮ ወንዝ ላይ በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተሰራ የብረት ተገጣጣሚ ድልድይ ለትራፊክ ክፍት ሆነ።
ዛሬ ተመርቆ ለአገልገሎት ክፍት የሆነው ድልድይ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ ከላሬ ኝንኛንግ በመገንባት ላይ ያለው የ34 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ አካል እንደሆነ ተነግሯል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት÷ ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ቢሆንም ህዝቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚውል በቂ መሰረተ ልማት የለውም።
በተለይም የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማት ተነፍጎት በመቆየቱ በሀብቱ መጠቀም ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁንም የጥራትና የፕሮጀክቶች በጊዜ ያለመጠናቀቅ የዘርፉ ማነቆ እየሆኑ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ከቅርብ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት በክልሉና በፌዴራል መንግስት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት ከፌደራል ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በባሮ ወንዝ ላይ በጊዜያዊነት ተገንብቶ ለትራፊክ ክፍት የሆነው ድልድይ የጅካዎና የላሬ ወረዳዎች ህዝቦች የዘመናት ጥያቄን የመለሰ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተወካይ ኢንጅነር መሰረት ደጀኔ በበኩላቸው÷ በክልሉ በአሁኑ ወቅት የአቦቦ ሜጢ፣ ጋምቤላ ኢሊያ ጨምሮ የአምስት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሁለት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የጨረታና የዲዛይን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ ብዙ የአስፓልት መንገዶች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶች በጥራትና በጊዜ ካለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የባለስልጣኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ተገጣጣሚ ድልድዩ የመንገዱንና በቋሚነት የሚሰራውን የ260 ሜትር የኮንክሪት ድልድይ ስራ ለማሳለጥ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ድልድዩ 180 ሜትር ርዝመትና ስድስት ሜትር ስፋት እንዳለውም ኢንጂነር መሰረት ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ድልድይ ባለመኖሩ በጀልባ በመሻገር ለተለያዩ ወጪ እና ከጀልባ አፈትልከው በመውደቅ ለተለያዩ ችግር ሲዳረጉ እንደነበር ተገልጿል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.