Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ለስድስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል ለስድስት ዓመታት በስምንት ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡

ፕሮጀክቱ የክልሉን ህብረተሰብ የልማት ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች ቢከናወኑም የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ የክልሉ ህዝብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሀገራችን ከተጀመረው አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመውና ጋምቤላን ጨምሮ 6 ክልሎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ስምንት ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ምርታማነትን በማሳደግና የገበያ ትስስር ችግርን በመፍታት፣ የማህበረሰቡን የመሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታትና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ጥናቶችን በማካሄድ የማህበረሰቡን ኑሮ ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፒተር ሆው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ 50 በመቶ ሴቶችና 20 በመቶ ወጣቶች ላይ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው በስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በክልሉ የተጀመረውን ልማት በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የጋምቤላ ክልል አስተባባሪ ዶክተር ቢየል ቢቾክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ለስድስት ዓመታት በ450 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚካሄድ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.