Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የስራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ መደረጉን የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ እንዳመለከተው በክልሉ የሙቀቱ መጨመር ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከየካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል።

በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል የመደበኛው የስራ ሰዓት ከጥዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ተኩል መሆኑን ተገልጿል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ 11 ተኩል የነበረው ከአስር ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል እንዲሆን መወሰኑን ምክር ቤቱ በመግለጫ አስታውቋል።

እንደ መግለጫው የስራ ሰዓት ለውጡ በማጃንግ ዞን የመንጌሽና የጎደሬ ወረዳዎችን አይጨምርም።

በለውጡ መሰረትም የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በተጠቀሰው የስራ ስዓት መስሪያ ቤታቸው በመገኘት የተለመደ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ምክር ቤቱ በመግለጫ አሳስቧል።

በብሄራዊ ሜቲዎሎጂ ኤጀንሲ የጋምቤላ ክልል አገልግሎት ማዕከል ዳሬክተር አቶ ሙሴ ትዛዙ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የክልሉ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ39 እስክ 40 ነጥብ 4 ድግሪ ሴሊሺየስ ሆኗል።

የለሊቱ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ደግሞ ከ21 እስከ 23 ድግሪ ሴሊሺየስ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.