Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በቀን 180 የኮሮና ቫይረስ ናሙናዎችን መመርመር መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት በሀገሪቱ የኮቪድ 19 መከሰቱ ከታወቀ ጀምሮ በጋምቤላ ክልል በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል፡፡

በክልሉ በርካታ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙና ከደቡብ ሱዳን ጋርም በሰፊው የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስን ለመመርመር የሚያስችል ማሽን ስራ እንዲጀምር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየተቱንም አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለያዩ ቦታዎች በተዘጋጁ የሙቀት ልየታ ያለምንም ፍራቻ ህብረተሰቡ ምርመራ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋትሉዋክ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር በክልሉ ቀደም ሲል ለኤች አይ ቪ መመርመሪያ ያገለግል የነበረው ማሽን አዲስ ሶፍት ዌር በመጫን ለኮቪድ 19 ምርመራ እንዲውል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ውጤቶችን ሲገልፁ እንደነበር ጠቅሰው በክልሉ ምርመራ መጀመሩ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ በተጨማሪ በክልሉ በተለያዩ ለይቶ ማቆያዎች ለሚገኙ ዜጎች በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል መናገራቸውን ከጋምቤላ ክልለ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመመርመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በክልሉ ከሚገኙ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.