Fana: At a Speed of Life!

በግድቡ ላይ በሚኒስትሮች ደረጃ በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የቆየው ድርድር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ. ቢ. ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለቀናት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ድርድር ተጠናቀቀ።
 
ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ በሁለት ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ የነበረበት ድርድሩ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎ ነበር።
 
ሚኒስትሮቹ ድርድራቸውን ዛሬ ሲያጠናቅቁ የጋራ መግለጫ በማውጣት መሆኑንም ነው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ማምሻውን የገለፁት።
 
በዋሽንግተኑ ውይይት ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የሁሉም ሀገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች፣ የውኃ ዘርፍ እና የህግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
 
በተጨማሪም የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ እና የአለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ተሳትፈዋል።
 
በድርድሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፥ በድርቅ ( Drought)፣ በአመታት የተራዘመ ድርቅ (prolonged drought) እንዲሁም በተራዘመ አመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት (prolonged periods of dry years) ወቅት የሚኖረው የአሞላል ሥርዓት ላይ መሰረታዊ መግባባት መደረሱን ነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
 
ስምምነት ያልተደረሰባቸው ቀሪ ጉዳዮች በቀጣይ ውይይቶች መፍትሄ የሚያገኙ ሲሆን፥ የሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ዝርዝር ረቂቅ ሰነድ እንደሚዘጋጅ ገልጿል።
 
በሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ላይ የሚደረገው ድርድር በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን፣ እንዲሁም የሀገራችንን ነባር እና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት የማይቀየር አቋም መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
 
በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እየተሰራ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ራስን ችሎ የመልማት መብት እንዲሁም የትብብር መገለጫ ነው ብሏል ሚኒስቴሩ።
 
መንግስት ግንባታውን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠውም ነው ብሏል።
 
መንግስት በቀጣይ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ አመልክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.