Fana: At a Speed of Life!

በጠ/ሚ ዐቢይ የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በአንበጣ መንጋ የደረሰውን ጉዳት ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በአንበጣ መንጋ ያደረሰውን ጉዳት ጎበኘ።

በጉብኝቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጉብኝቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ፥

“ባለፉት ወራት ከኮቪድ19 በተጨማሪ ካጋጠሙን ከባድ ፈተናዎች መካከል አንዱ፣ ኢትዮጵያን እና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃው የበረሀ አንበጣ ነው” ብለዋል።

አደጋው የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል መንግሥት ዘርፈ ብዙ ርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

“ሁለተኛ ዙር የአንበጣ መንጋ ወረራን በተጋፈጥንበት በዚህ ወቅትም እንዲሁ ሁኔታውን ለመቆጣጠር እንዲቻል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

ዛሬ አንበጣ ያደረሰውን ጉዳት እና እየተወሰደ የሚገኘውን የመከላከል ርምጃ፣ ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ተገኝተው መመልከታቸውን አስታውቀዋል።

“አርሶ አደሮቹ ያለባቸውን ወቀታዊ ችግር አድምጫለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ቃል ገብቼላቸዋለሁ” ብለዋል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዘጠኝ ሺህ ሄክታር የማሽላ ሰብል በማውደሙ አርሶ አደሩ ለችግር መጋለጡ ከዚህ በፊት የዞኑ ግብርና መምሪያ መግለጹ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.