Fana: At a Speed of Life!

በጠ/ሚ ዐቢይ የተቋቋመው ብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ወደ ስራ ገብቷል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው ብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ስራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
 
የኮሚቴው ሰብሳቢ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ ኮሚቴው “የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በተባበረ አቅም መመከት ይቻላል!” በሚል መሪ ቃል ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
 
ብሔራዊ ዓብይ ኮሚቴው 10 አባላት እና 4 ንዑሳን ኮሚቴዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ አባላቱ የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመስጠት ስራ ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።
 
የተቋቋመው ኮሚቴ በተለያየ መልኩ ሲከናወን የነበረውን ሃብት የማሰባሰብ ሂደት ወደ ተቀናጀ አሰራር በማምጣት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በዚህ መሰረትም ሃብት የማሰባሰብ ስራውን በተሳካ ሁኔታ ለማሳለጥ ኢትዮ ቴሌኮም ካዘጋጀው አማራጭ በተጨማሪ በ13 ባንኮች ገንዘብ መሰብሰብ የሚያስችሉ የባንክ ቁጥሮች መከፈታቸውን ተናግረዋል።
 
ከዚህ ባለፈም በአይነት የሚደረጉ ድጋፎችን ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።
 
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የዓለም ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መግታት ይቻል ዘንድ ሁሉም የህብረሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
በበርናባስ ተስፋዬ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.