Fana: At a Speed of Life!

በጣና ሐይቅ ላይ ተንሳፎ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው የእምቦጭ አረም ሙሉ ለሙሉ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጣና ሐይቅ ላይ ተንሳፎ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው የእምቦጭ አረም ሙሉ ለሙሉ መሰብሰቡን የጣናና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የጣናና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ ÷የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በዚህ ዓመት የፌዴራልና የክልል መንግሥት የተለየ ንቅናቄ ፈጥረው በተለይ በ2013 ዓ.ም መቶ በመቶ በዓይን የሚታየውን አረም ለማስወገድ እንቅስቃሴ ጀምረው ጥሩ ውጤትም አምጥተዋል።

ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር አያሌው÷ በአሁኑ ወቅት በሐይቁ ዳርቻ እስከ ሁለት ሜትር ድረስ ይንሳፈፍ የነበረውን አረም በማስወገድ አረሙን ማከማቸት ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የሚሰራው ሥራ ውጤቱ በዓይን የማይታይ ነበር አሁን የሐይቁ አካል ለዋና፣ ለዓሣ ማስገርና ለመጠጥነት ለመዋል ምቹ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ አረሙ መቶ በመቶ ተወግዷል ማለት ባለመሆኑ የተከማቸው አረም ተገላብጦ መቃጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

አረሙን ከተጠራቀመበት የማጠናቀቅ ሥራ መቅረቱን በመጥቀስም ማጠናቀቅ ካልተቻለ የመመለስና የመስፋፋት ዕድሉ እንዳለ መሆኑን አስረድተዋል።

አረሙን ለማገላበጥ የሚውለው ማሽን በሰዓት ከ1 ሺህ 500 ብር በላይ የሚያስከፍል በመሆኑና ኤጄንሲው የገንዘብ እጥረት ስላለበት ክረምት ከመምጣቱ በፊት ስራውን ለማጠናቀቅ በተለይ የፌዴራልና የክልል መንግሥትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ቃል የገቡትን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡም በቀን የሚከፈለውን 150 ብር ከቁም ነገር ቆጥረው አረሙን ቶሎ ከማስወገድ ይልቅ የማቆየትና የማስፋፋት ሥራ እንዳይሰሩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የገበታ ለሃገር ፕሮጀክትም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይሰራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉና ሐይቁን ከመጠበቅ አንጻር የጎንደር ዩኒቨርሲቲም የጐርጐራን መሪ እቅድ ፕላን ሲያወጣ የጣናን ትልቁን ሀብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንዲሆንም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሐይቁን ከመከለልና እምቦጭን ከማጥፋት ባለፈም እንደ ደንገል፣ ፊላ፣ ዶቅማና የመሳሰሉ ነባር ሀገር በቀል እጽዋት መተከል አለባቸው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.