Fana: At a Speed of Life!

በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ገንዘብ ወደ ግለሰብ አካውንት ያዛወሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራ አባላት ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰቡትን ገንዘብ በማጭበርበር ወደ ሌላ የግለሰብ አካውንት እንዲገባ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ፡፡
በአሜሪካ እና በጀርመን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ይዉል ዘንድ ከራሳቸው፤ ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ያሰባሰቡትን የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶችን በማጭበርበር በግለሰብ አካውንት ውስጥ በማስገባት የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዳያስፖራ አባላቱ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ለገሀር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲያስፖራ ቅርንጫፍ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ሲሞክሩ የባንኩ ሰራተኞች በተባለው አካውንት ያስገቡ በማስመሰል ወደ ሌላ ግለሰብ አካውንት ገቢ ካደረጉ በኋላ ይህንኑን ደረሰኝ ለዳያስፖራ አባላቱ ሰጥተዋል።
በዚህ መሰረት የዳያስፖራ አባላቱ ገንዘቡ ገቢ የተደረገው ወደ ግለሰብ አካውንት መሆኑን በማረጋገጣቸው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውንና ፖሊስም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የወንጀል ምርመራ ቢሮው ገልጿል፡፡
የዳያስፖራ አባላቱ ለፖሊስ ለሰጡት ጥቆማ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።
በቀጣይም እንደነዚህ አይነት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የተለመደውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡን ከኢትዮፕያ ፌዴራል ፖሊስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.