Fana: At a Speed of Life!

በጦር ግንባር እያደረግን ያለውን ተጋድሎ በመደበኛ ስራዎችም በተመሳሳይ ወኔና እልህ እንደግመዋለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ግንባሮች ባስገኘናቸው ድሎች ወራሪው ሃይል ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደማይችል ይሄ ትውልድ በተግባር አስመስክሯል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
 
በአዲስ አበባ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የመደበኛ ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ በወቅታዊ ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
 
በውይይት መድረኩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የገጠመንን የህልውና ፈተና ለመመከት የምናደርገው ትግል መደበኛ አካል በመሆኑ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተከፈተብንንም ጦርነት ከማሸነፍ ጎን ለጎን መደበኛ ስራችንን ማስኬድ አለብን ብለዋል።
 
በዚህም በቀረበው ሪፖርት ላይ የተጋረጠብንን ፈተና ለመመከት ከተደረገ ድጋፍ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ጦርነቱን ለማሸነፍ በተከናወኑ መደበኛ የገቢ አሰባሰብና ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገ የምርት አቅርቦት ስራዎች ላይ የተገኘዉ ዉጤታማነት በሌሎች ተቋማትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።
 
አዲስ አበባ የጥፋት ኃይሎች ዋነኛ ኢላማ ሆና ባለበት ሂደትውስጥ፣ የጥፋት ሃይሉን ከንቱ ምኞት አምክኖ መደበኛ ስራዎችን በታለመላቸው ጊዜ እየተተገበሩ እንዲሄዱ ለማስቻል የተሰሩ የክትትልና ድጋፍ አግባቦች ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
 
በከተማዋ ባለፉት 4 ወራት 25 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱ የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ አገር ወዳድነት የሚያሳይ ተግባር ነው ብለዋል ከንቲባዋ።
 
ከአሸባሪው ቡድን ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት የተጀመረው የቅንጅት ስራ አካል በመሆን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ድጋፋችንን አጠናክረን ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
 
በተለያዩ ግንባሮች ባስገኘናቸው ድሎች ወራሪው ሃይል ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደማይችል ይሄ ትውልድ በተግባር አስመስክሯል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች።
 
በዚህም እንደ ሀገር የተቃጣብንን ጥቃት ለመመከት ለመከላከያ ሰራዊቱና ለጸጥታ ሃይሎች ስናደርግ በቆየነው ድጋፍ የዚህን ትውልድ ታሪክ በሚገባ ጽፈናል፤ የዚህ ትውልድ አካል በመሆናችንም ልንኮራ ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
የተገኘውን ድል በማስቀጠል ሀገራችን ተገዳ የገባችበትን ጦርነት በድል እንድትወጣ በማድረግና የወደሙ ቦታዎችን መልሶ በማቋቋም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ተረጋጋ የቀድሞ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስም ከመደበኛዉ የከተማ ስራ ጎን ለ ጎን የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.