Fana: At a Speed of Life!

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራ ልዑክ ከዓለም ባንክ አመራሮች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አክሴል ቫን ትሮትሴበርግ እና ከባንኩ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዚዳንት ሀፊዝ ግሀኔም ጋር በፈረንሳይ ፓሪስ ውይይት አድርጓል።

በኮቪድ19 ምክንያት የተዳከመውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አነሳሽነት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ፈረንሳይ ፓሪስ የተገኘው ልዑክ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን ትብብር ለማስቀጠል እንዲቻል ያለመውን ውይይት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በተገኙበት ተካሄዷል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከዓለም ባንክ በምታገኛቸው ድጋፎች ያላትን አፈፃፀም በተመለከተ ገለፃ ለማድረግ ማስቻሉን ውይይቱን የተከታተሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ያስሚር ወሀቢረቢ ገልፀዋል።

የዓለም ባንክ የአምስት አመት መሪ የመሰረተ ልማት እቅዶችን መሰረት በማድረግ የሚሰጠውን ብድር በቀጣይ ዙር እንዴት ለመጠቀም ታስቧል የሚለውን ጉዳይም ማስረዳት ተችሏል ብለዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር ያላትን ትብብር ለማስቀጠል የሚያስችላት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

ማክሰኞ የሚካሄደው ፈረንሳይ የአፍሪካ መሪዎች በኮቪድ19 ምክንያት የተዳከመው ኢኮኖሚያቸው እንዲያንሰራራ ያዘጋጀችው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ጉባኤ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጊኒ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ አንጎላ ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል እና ኮትዲቯር ተሳታፊ መሆናቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚሳተፉበት በዚህ ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ሊቀመንበር አኪንውሚ አዴሲናም ተሳታፊ ናቸው።

ጉባኤው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳው የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ መፍትሄ ማፈላለግን አላማው አድርጓል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.