Fana: At a Speed of Life!

በ2011 ዓ.ም በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የደረሰው አደጋ የመጨረሻ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ ይሆናል- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2011 ዓ.ም በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የደረሰው አደጋ የመጨረሻ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውም የሚታወስ ነው።

ሚኒስቴሩም በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች 2ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው  በአለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (CAO) ተቀፅላ 13 ንዑስ አንቀፅ 6.6 እና የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ደንብ ክፍል 6.1 መሰረት አንድ የአይሮፕላን አደጋ የምርመራ ሪፖርት በ12 ወራት ውስጥ ለህዝብ የማይገለፅ ከሆነ አደጋው የሚዘከርበት ዓመት የምርመራ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ አደጋውን ለመርመር ኃላፊነት ያለበት ሀገር ማሳወቅ እንዳለበት እንደሚደነግግ አስታውሷል።

በዚሁ መሠረት በበረራ ቁጥር ኢቲ-802 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር መጋቢት 1 ቀን 2011 ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ከአዲስ አበባ ቦሌ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 28 ኖቲካል ማይልስ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጊምቢቹ ወረዳ ልዩ ስሙ ኤጄሬ በተባለ ቀበሌ ወድቆ መከስከሱና አሳዛኝ አደጋ መድረሱን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ባለው የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ በICAO ተቀፅላ 13 መሰረት እና በአውሮፕላን አደጋ ምርመራ አዋጅ ቁጥር 957/2008 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የምርመራ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው ወቅቱን በመጠበቅ የቅድመ አደጋ የምርመራ ሪፖርትና ቀጣይ ሂደቱ ያለበትን ደረጃ የሚገልፅ ሪፖርት ሲያሳውቅ መቆየቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የምርመራ ሂደቱ የደረሰበትን የመረጃ ሪፖርት የማሳወቅ ስራ ከተሰራ በኃላ  በዓለም አቀፍና በሀገሪቱ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የምርመራ ሂደቱ የዘገየ ቢሆንም ቢሮው ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃዎች እየወሰደ የምርመራ ስራውን በማስቀጠሉ የምርመራ ሂደቱን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ለማድረስ ተችሏል ብሏል፡፡

በመሆኑም የትራንስፖርት ሚኒስቴር የበረራ ቁጥር ET-302 አስመልክቶ የመጨረሻውን ሪፖርት እና በቀጣይ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች በይፋ በቅርብ ጊዜ የሚያሳወቅ መሆኑን ገልጿል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.