Fana: At a Speed of Life!

በ2013 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተያዘው የ2013 በጀት አመት ከአገራዊ ወጪ ንግድ 3 ነጥብ 91 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት በእቅድ መያዙን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል ከሚያደርግባቸው የግብርና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ውስጥ 2 ነጥብ 918 ቢሊየን ከግብርና እና 587 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን ደግሞ ከማኑፋክቸሪንግ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።

ከዚያም ባለፈ ሚኒስቴሩ ከምርት አቅርቦት እስከ ወጪ ንግድ ባለው የግብይት ሰንሰለት በየደረጃው ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተግዳሮቶችን በቅንጅት በመፍታት ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሳደግ ዓላማው መሆኑንም አስታውቋል።

ይህንን መሰረት አድርጎም የኮቪድ-19 ወረርሽን ለግብርና ምርቶች ያለው አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅእኖን ጨምሮ የአምስት ዓመታት የግብርና ምርቶች የምርት እና ምርታማነት ትንተና፣ የአምስት ዓመታት የወጪ ንግድ የዕቅድ አፈፃፀም ትንተና ፣የ2012/13 ምርት ዘመን የግብርና ምርቶች አቅርቦት ትንበያ ግምት፣የግብርና ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ያላቸው ፍላጎት እና ሌሎችም ጉዳዮችን ለተዘጋጀው እቅድ በመነሻነት የታዩ መሆናቸው ተመላክቷል።

እቅዱን ለማሳካትም የምርት አቅርቦትንና ጥራትን ማሳደግ ፣ የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል፣ የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻል የህገ- ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መቆጣጠር እና የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚተገበሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.