Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ የአራራት ኮተቤ የአስፓልት መንገድን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግንባታው ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የአራራት ኮተቤ የአስፓልት መንገድ በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

መንገዱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሎ ከሶስት አመት በፊት ድሪባ ደበርሳ እና ተክለብርሃን አንባዬ ተቋራጮች በሲጥም እስካሁን አልተጠናቀቀም።

የግንባታው ሂደት ከታሰበው ጊዜ በላይ በመውሰዱም የአካባቢው ነዋሪ ከጠበቀው በተቃራኒ እንግልትን እንዲሸከም ሆኗል።

በተለይ ሁለተኛው ምዕራፍ ማለትም ከአራራት ኮተቤ ድረስ ያለው መንገድ ተቆፋፍሮ ለእግረኛውም ለተሽከርካሪም አጋዳች እንደሆነ ነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገበት ወቅት የተመለከተው።

አስተያየታቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ ነዋሪዎችም፤ መንገዱ ተቆፋፍሮ ለረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገናል ብለዋል።

በአካበቢው የሚሰሩ አሽከርካሪዎችም የመንገዱ ወጣ ገባነት የተሽከርካሪ እቃዎችን እየሰበረ ለወጪ መዳረጋቸውንና በስፍራው ለተለየዩ አደጋዎች መከሰትም ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር ኢንጂነር ታከለ ሉላና፥ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ክፍል በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን በመግለፅ፤ የመንገዱን 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሁለተኛው ክፍል ግን የአፈጻፀም ችግር እንዳለበት ተናግረዋል።

ተቋራጩ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ የተሰጠው ቢሆንም ተጨባጭ ለውጥ ባለማምጣቱ የመጨረሻ የሆነውን የማስቆም እርምጃ ተወስዶበት  አሁን የመንገዱ ግንባታ በተቋሙ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።

የርክክብ ስራውን በማጠናቀቅ ጎን ለጎን የዝግጅት ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም በበጀት አመቱ መንገዱን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ባለስልጥኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው መንገዱ ሲጠናቀቅ የትራፊክ ፍሰቱን እንደሚያስተካክልና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

5 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ለዚህ መንገድ ከ260 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት ነበር ወደ ስራ የተገባው፡፡

በማርታ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.