Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት እንደ ሀገር መቀጠል የማንችልበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳችን ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡

ህዝብን በጸረ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመምራት የሚደረግ አይን ያወጣ ተጽዕኖ፣አድርግ ወይም አታድርግ በሚሉ ቃሎች ብቻ የተገደበ እና ህዝብን ለማሸማቀቅ በርካታ ድርጊቶች ሲፈፀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ህዝብን ከፋፍሎ የመግዛት አባዜ የተጸናወተው ጥቂት የህወኃት ቡድኖች በርካቶች ተገፍተው ከሀገር እንዲወጡም ምክንያት ነበሩ፡፡

ለሀገራቸው ፖለቲካ ያገባናል ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች ሀሳባቸውን አውጥተው መግለጽ እንዳይችሉ ሲደረግባቸው የነበረውን አፈና፣እስር፣ግርፋት እና አሰቃቂ ድርጊቶች ለፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ እንደምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የመሰረተ ልማት እጥረት ባልተቀረፈበት እና የህዝብ የልማት ጥያቁዎችን መፍታት አዳጋች በሆነባት ሀገር እነዚሁ አጥፊ ቡድኖች በርካታ የህዝብና የመንግስት ተቋማትን በመዝረፍና የዘረፉትን ወደ ውጭ ሀገራት በማሸሽ በህዝብ ላይ ክህደት በሀገር ላይ የኢኮኖሚ ውድቀት አስከትለዋል፡፡

እወክለዋለሁ ላለው የትግራይ ህዝብ በተጨባጭ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የተሳነው ይህ አጥፊ ቡድን ከሀገራዊ ለውጡ እኩል መራመድ ባለመቻሉና ሲፈፅማቸው የነበሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች ከህዝብ ፊት መቆም እንዳይችል ስላደረገው ውህደቱን ከመቀላቀል ይልቅ መግፋትን አማራጩ አድርጓል፡፡

ለህገ መንግስታዊ ስርዓት ጠበቃ ነኝ ሲል የነበረው አጥፊው የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ለመነጣጠልና ለህገ መንግስቱ ያለውን ንቀት ያረጋገጠበትን ሀግ ወጥ ክልላዊ ምርጫ ሲያደርግና ህጋዊ ያልሆነ መንግስት ሲመሰርት በሆደ ሰፊነት የተመለከተው የፌደራል መንግስት ይህ ቡድን እየተከተለው ያለው ኢ-ህግ መንግስታዊ አካሄድ ከዛሬ ነገ ሊለወጥ ይችላል በሚል ጊዜ ሰጦት ቆይቷል፡፡ ዳሩ አምባገነናዊ ባህሪው እያደገ ቢመጣም፡፡

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሀገራዊ ለውጡ በጋራ ለመቆም ፍላጎት ቢኖረውም ጥቂት የህወኃት ቡድን አመራሮች ግን የህዝቡን ፍላጎት ወደ ጎን በመግፋት ህዝቡ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖረው ጭቆና ሲያደርስበት ቆይቷል፡፡

ብልጽግናና የለውጡ መሪዎች ህወኃት ውህደቱን እንዲፈጽምና ለጋራ ሀገራችን በጋራ እንቁም መርህ በተደጋጋሚ ጊዜ የድርጀቱን መሪዎች በማግኘት ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ማወያየት ቢቻልም ወትሮውንም ሀገርንና ህዝብን የማገልገል ጽኑ ፍላጎት ሳይሆን በስልጣን የሚገኝ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ጥያቄያቸው ለውህደቱ እምቢታቸውን አሳይተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋ ያልቆረጡት የለውጡ መሪዎች በህዝብ የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ የትግራይን ህዝብ ከለውጡ ጋር አብሮ ለማስቀጠል ያላሰለሰ ግፊት ቢደረግም በጸረ ለውጥ ቡድኖች ሰንኮፍነት እንደታሰበው ውህደቱን ለማቀላቀል የተደረገው ጥረት ያለ ውጤት ተጠናቋል፡፡

መቀሌ የመሸገው የጥፋት ቡድኑ ምስኪኑን የትግራይን ህዝብ ጠዋት ማታ የአማራ ክልልና የፌደራል መንግስት ጦርነት በህዝባችን ላይ ሊከፍቱብን ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ ህዝቡን በማደናገር እረፍት አሳጥቶት ከርሟል፡፡

የትግራይ ህዝብ ጦርነት እንዳንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልብ ይረዳዋል፡፡

ጦርነት የመጨረሻ እንጂ የመጀመሪያ አማራጭ እንዳልሆነ ብልጽግና ይገነዘባል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱን ከክልሉ ፈቃድ ውጭ ማደራጀት አትችሉም የሚል አቋም እየተከተለ ያለው ሴረኛውና ጥቂቱ የህወኃት ቡድን የፌደራል መንግስትን ውሳኔዎችና የሚሰጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እንዳይሆኑ ግትር አቋሙን ሲያሳይ ቆይቷል ፡፡

ከህዝብ አብራክ ወጥቶ ህዝብንና ሀገርን ከጥቃት እየተከላከለ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊቱን የቆዬ ክብርና ዝና ለማጠልሸት ሲሞክር ሆደ ሰፊው ሰራዊት ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ለጥፋት ሁሌም የማይተኛው ጥቂት የህወኃት ቡድን አማካኝነት በተሰጠው ትዕዛዝ በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕና ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ላይ ትናንት ሌሊት ጥቃት ከማድረሳቸው ባሻገር ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርገዋል፡፡

ነገሩን በሆደ ሰፊነት ሲመለከተው የቆየው መንግስት እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶች ገደብ በማለፋቸውና ግልጽ ትንኮሳ በመፈጠሩ ምክንያት ይህንኑ ድርጊት ሊመክት የሚችል አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል፡፡

በዚህ መሀል ምንም የማያውቀው የትግራይ ህዝብ ተጎጂ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ሁሉ ብልጽግና ፓርቲ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን የሚሰራና የህዝብንና ሀገርን ሰላም አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ማናቸውንም ነገሮች ለመታገስ እንደማይችል ታዉቆ በተሣሣተ መረጃ ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ ላይ ያልተገባ ስጋት በመፍጠር ተጠራጣሪ ለማድረግ የሚደርገው ተከታታይ ቅስቀሳ የትግራይ ህዝብ ሊያወግዘው የሚገባ መሆኑን በፅኑ በማመን የሚከተሉትን የአብሮነትና የአጋርነት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

1. ለተከበርከው የትግራይ ህዝብ

የትግራይ ህዝብ ከሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ጠንካራ ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ-ጭቆና ትግል ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የሀገረ መንግስት ምስረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ህዝቦች ናቸው፡፡

ሆኖም የሕወሓት አጥፊ ቡድን የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ የትግራይን ህዝብ የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እያቀረብን በዚህ አሸባሪ ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል ውስጥ ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናርባለን፡፡

2. ለመላው የትግራይ ምሁራን

ሀገርን በሚፈለገው ደረጃ መለወጥ ካስፈለገ ምሁራን የሚያደርጉት አስተዋጾኦ ከፍ ያለውን ቦታ መያዙ ግልጽ ነው፡፡

ሆኖም ግን ህወኃት በክልሉ የሚገኙ ምሁራንን ለሀገራቸው ሁለንተናዊ አበርክቶ እንዳያደርጉ በጥቅም የተሳሰረው ቡድን እንቅፋት እንደሆነባችሁ መረዳት ተችሏል፡፡

ስለሆነም ምሁራን በነጻነት ተንቀሳቅሰው ያላቸውን አቅምና ዕውቀት ለሀገራችን ህዝቦች እንዲያበረክቱ ካስፈለገ ጨቋኙንና ጸረ ለውጡን የህወኃት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም የተከበራሁ በትግራይ የምትገኙ ምሁራን ሁላችሁም የፌደራል መንግስት በክልሉ እያደረገ ያለው ህገ መንግስቱን ማስከበር ስራ በውጤታማነት ለመፈፀም እንዲቻል የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ የአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋልን፡፡

3. ለመላው የትግራይ ወጣቶች

በክልሉ የምትገኙ ወጣቶች ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ሳትችሉ ነገር ግን በስማችሁ እየተነገደ ለበርካታ ዓመታት ቆይታችኋል፡፡ይህንን አይን ያወጣ ዘረፋና ሌብነት በአጥፊ የህወኃት ቡድን አማካኝነት ሲካሄድ እንደነበርም የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

በስሙ ሲነገድበት ለቆየው የትግራይ ወጣት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ ዘንድ በዚህ አጥፊ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልና መላው የትግራይ ወጣቶች በፌደራል መንግስት በኩል እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር እርምጃ በመደገፍ ለክልሉና ለሀገር ሰላም አጋር እንድትሆኑ የትግራይ ወጣቶች ከመላው የሀገራችን ወጣቶች ጋር በመሆን የጀመርነውን አገራዊ ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

4. በትግራይ ክልል ለምትገኙ የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች

የትግራይ ክልል የፀጥታ ሀይሎች በሀገሪቱ ከሚገኙ የፀጥታ ሃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ህዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉአላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን ብልጽግና ፓርቲ ከልብ ይገነዘባል ፡፡

ምንም እንኳ በክልሉ አምባገነን የሆነው የህወኃት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን እንግልትና ስቃይ የታዘባችሁ ቢሆንም ባለው ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ምክንያት ለውጡን ከህዝባችሁ ጋር ሆናችሁ ማጣጣም ሳትችሉ ቀርታችኋል፡፡

ሆኖም ለረዥም ዓመታት የክልሉን ህዝብ ሰላም ደህንነት በሀላፊነት መንፈስ ወስዳችሁ ስትጠብቁ የቆያችሁ የክልሉ ፖሊስ፣ ልዩ ሀይል አባላትና ሌሎችም በህዝብ ትክሻ ላይ ሆኖ እየቀለደ ባለው ዘራፊና አጥፊ የህወኃት ቡድን ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለውን ትግል በመቀላቀል ህዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
ጥቅምት 25/2013 ዓ/ም
አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.