Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ በሩሲያ ገዢ ፓርቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የኢንተርኔት ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሩሲያ ገዢ ፓርቲ ብልፅግናን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ገዢ ፓርቲዎች ጋር የኢንተርኔት ኮንፈረንስ አካሄደ።
በሩሲያው “ዩናይትድ ሩሲያ” ፓርቲ አዘጋጅነት የተዘጋጀው ይህ ኮንፈረንስ የኢትዮጵያው ብልፅግና፣ የደቡብ አፍሪካ ኤ. ኤን.ሲ፤ የናይጄሪያ ኤ.ፒ ሲ፣ የአልጄሪያ ኤፍ ኤል ኤን ፓርቲን ጨምሮ 13 አፍሪካ ሀገራት ገዢ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ነበር።
የኮንፍረንሱ ዋና አላማ ፓርቲ ለፓርቲዎችን ግንኙነት ማጠናከር ሲሆን በመድረኩ የፓርቲዎች መሰረታዊ እሳቤና አገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ የኮሮና ቫይረስና የወደ ፊት የፓርቲዎቹ ሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የግንኙነት አግባብ ላይ ምክክር መደረጉን የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በኮንፍረንሱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፥ ፓርቲው የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ ለመመለስ እራሱን በአዲስ መልክ መደራጀቱን ገልጸዋል።
ፓርቲው ገና ከምስረታው ጀምሮ በሀገሪቱ በርካታ የፖለቲካ ሪፎርሞችን መከወን መጀመሩንና የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት ላይ በርካታ ተጨባጭ ስራዎችን መስራቱን አስረድተዋል።
ፓርቲው ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ፤ አቃፊነትንና ወንድማማችነትን ቀዳሚ መርህ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ያብራሩት ዶክተር ቢቂላ፥ በዚህ አካሄዱ ለህዝቡ ቃል የገባውን ዴሞክራሲዊትና የበለጸገች ሀገር እውን የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ይህን ለማድረግ የሚያስችለው የፓርቲ አደረጃጀት የመፍጠርና ብቁ አመራርና አባል የማፍራት ስራም በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጎላ ጉዳት እንዳያደርስም መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃዎችም ለኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
የሩሲያው ገዢ ፓርቲ ምክትል ጸኃፊና የአለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽነር አንድሬ ክልሞቭ በበኩላቸው፥ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ከሆነው ብልጽግና ጋር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ አበባ ላይ መድረኮችን እንደሚያካሄዱና ኢትዮጵያንም እንደማዕከል እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.