Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በምርጫው የጎላ የፀጥታ ችግር አለመከሰቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው ሃገር ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የጎላ የፀጥታ ችግር አለመከሰቱን አስታወቀ፡፡

ቆጠራ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎችም ውጤት ከዚህ ምሽት ጀምሮ ይገጻል ተብሏል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በአብዛኛው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎችም ወደ ድምጽ ቆጠራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከተከሰተው መጠነኛ ችግር ውጭ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁንም አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በስጋት ምስራቅ ሐረርጌ ዞን አንድ ምርጫ ጣቢያ አለመከፈቱን እንዲሁም ምዕራብ ሸዋ ዞን ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች በተከሰተ ችግር መዘጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጅ በአብዛኛው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ውጤታማ እንደነበርም አንስተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ በአንዳንድ አካባቢዎች ከተፈጠረው የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ጋር በተያያዘም ቦርዱ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የተፈጠረውን እጥረት መቅረፍ ሲቻል፥ በሲዳማ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት መፈጠሩን አውስተዋል፡፡

በተለይም በሲዳማ የተፈጠረውን የድምጽ መስጫ ወረቀት ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት በተፈለገው ጊዜ ማድረስ ባለመቻሉ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲቋረጥ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም በነገው እለት ረፋድ ላይ በሲዳማ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ወረቀት ስርጭት ተደርጎ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በጋምቤላ በአምስት የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ እጥረት በማጋጠሙ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተቋርጦ እንዲቆይ መደረጉን ጠቅሰው፥ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ግን መደበኛው ሂደት መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል አሶሳ ሆሃ እና አሶሳ መጋሌ የምርጫ ክልል የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ምርጫው ተቋርጧልም ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፡፡

አሁን ላይ የምርጫ ቁሳቁስ በተለያዩ አማራጮች በስፍራው በመድረሱ በነገው ዕለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የሚካሄድበትን ሁኔታ ቦርዱ ይወስናል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ለተፈጠረው የቁሳቁስ ስርጭት እጥረት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

በአማራና ደቡብ ክልሎች የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎችን በተመለከተ አቤቱታዎች መቅረባቸውን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍጥነት እንደሚጣራም ገልጸዋል፡፡

በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ 44 ሺህ የሃገር ውስጥ ታዛቢዎች መሰማራታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ ከ200 በላይ ደግሞ የውጭ ታዛቢዎች ዕውቅና አግኝተው ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.