Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በኦነግ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትን አስመልክቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትን አስመልክቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አካላት መካከል ተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲደርሱት እንደነበር ይታወቃል፡፡

የፓርቲው የተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ አባላት ነሃሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈ እና በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱ ሊቀመንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ አሳውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ አመራር ላይ ተከታታይ አቤቱታዎች አስገብተዋል፡፡

በሌላ በኩል የድርጅቱ ሊቀመንበር መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከሃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን ለቦርዱ አስታውቋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሣኔ ሃሣብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባኤ የማቋቋም ሥልጣን አለው፡፡

በህግ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት በማድረግም የሁለቱንም ቡድኖች ደብዳቤዎች እና አቤቱታዎች የሚያይ የባለሙያዎች ኮሚቴ ለማቋቋም ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረት በእነ አቶ አራርሶ በኩል ባለሙያ ቢመድቡም በእነ አቶ ዳውድ በኩል ባለሙያ ለመመደብ ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ በፓርቲው የውስጥ ደንብ መሰረት መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ቦርዱ ይህንን ጉዳይ ለማየት ፈቃደኛ የሆነ ባለሙያ ለማግኘት አልቻለም፡፡

በመሆኑም ቦርዱ በራሱ ጉዳዩን መርምሮ ለመወሰን ተገዷል፡፡

ቦርዱ ጉዳዩን በመመርመር ሂደት በሁለቱም ወገን ያሉ የፓርቲው አመራሮችን አነጋግሯል።

ሁለቱም ወገኖች የጠቀሱት የፓርቲው ስነስርአት እና ቁጥጥር ኮሚቴንም ጠርቶ አወያይቷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የፓርቲው ስነስርአት እና ቁጥጥር ኮሚቴ ከላይ በተጠቀሱ እግዶች ዙሪያ ውሳኔ መስጠት እንደማያስፈልገው ገልጿል፡፡

ከዚህ በመነሳትም በአመራሮቹ መካከል ያለው አለመግባባት በፓርቲው ውስጥ እንደማይፈታ እና የቦርዱን ውሳኔ እንደሚፈልግ በመረዳት የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች ቦርዱ ወስኗል፡፡

1. ቦርዱ በድርጅቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አራርሶ ቢቂላ ፊርማ የተላከለትን የድርጅቱን ሊቀመንበር የታገዱበትን ስብሰባ የሚገልጸውን ቃለጉባኤ ተመልክቶ በቃለ ጉባኤው ላይ የተገኙት ስራ አስፈጻሚ አባላት ከስምንቱ አምስት መሆናቸውን ከአምስቱ መካከልም አንዱ አባል ከዚህ ቀደም በዜግነታቸው የተነሳ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተቀነሱ በመሆናቸው ስራ አስፈጻሚው ስብሰባ የሚጠበቀውን 2/3 ምልአተ ጉባኤ ያልተሟላበት መሆኑን ተረድቷል፡፡

በመሆኑም ከድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ የተላከው የሊቀመንበሩ እገዳ ውሳኔ ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ወስኗል፡፡

2. በአቶ ዳውድ ፊርማ የተከናወነው እና የብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ ነው ተብሎ ለቦርዱ የቀረበው የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከሃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ የተወሰነው ውሳኔ ስብሰባው በትክክል መካሄዱን የሚያሳይ ቃለጉባኤ የሌለው፣ ምን ያህል የምክር ቤት አባላት እንደተሳተፉበት እና በምን አይነት ድምጽ አሰጣጥ (አብላጫ ድምጽ የተወሰነ መሆን አለመሆኑን) የማያሳይ በሊቀመንበሩ ፊርማ ብቻ የተላከ ውሳኔ በመሆኑ ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት የፓርቲው ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ስራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

3. ቦርዱ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ባደረገው ውይይት ሁለቱም ወገኖች የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በታህሳስ 2013 ዓ.ም መደረግ እንደሚገባው ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የወሰነ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡

በቦርዱ መስፈርት መሰረትም ኦነግ እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ከሚገባቸው ፓርቲዎች አንዱ ነው፡፡

በተጨማሪም አሁን ባለው አለመግባባት የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ሃላፊነታቸውን በመወጣት የአባላቶቻቸውን እና የፓርቲውን ጥቅም የሚያስጠብቁበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑም በግልጽ ይታያል፡፡

በዚህ የተነሳም ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ሁለቱም ቡድኖች በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያከናውኑ ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ለዚህ ዝግጅት ሁለቱም ወገኖች የሚገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባቸውንም በቦርዱ ስብሰባ አዳራሽ እንዲያከናውኑ የተወሰነ ሲሆን ጊዜው ለሁለቱም አመራሮች የሚነገር ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ታህሳስ 09 ቀን 2013 ዓ.ም

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.