Fana: At a Speed of Life!

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል-የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማይቋረጥ ልምድ ጠቀሜታ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በስፋት እየተስተዋለ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑና ተያያዥ በሽታዎችን ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማይቋረጥ ልምድ ጠቃሚ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ 41 ሚሊየን ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ 15 ሚሊየን የሚሆኑት ከ30 እስከ 69 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ይነገራል።

በኢትዮጵያ የጤና እክል ከሚገጥማቸው ሰዎች መካከል 51 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከተቻለ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር የሚቀንስ መሆኑንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2020 ያደረገው ጥናትም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር በበሽታ የመያዝ አጋጣሚን ከ6 እስከ 32 በመቶ ሲቀንስ የመድኃኒት ወጪንም ከ20 እስከ 55 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል አረጋግጧል።

በጥናት እንደተረጋገጠው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ሰዎች በሥራ ውጤታማነታቸው በአማካይ 52 በመቶ ተጨማሪ ስኬት የሚያስመዘግቡ ይሆናል።

በኢትዮጵያም ዜጎች ጤናቸውን እየጠበቁ በየሥራ መስካቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር እንዳለባቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አሳስቧል።

በሚኒስቴሩ የማህበረሰብ ስፖርትና ተሳትፎ ዳይሬክተር ተስፋዬ በቀለ፥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል መንግስት በፖሊሲ ታግዞ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሚፈለገውን ስኬት ለማምጣት ግን የመንግስት ጥረት ብቻ በቂ ባለመሆኑ የማህበረሰቡ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በስፋት እየተስተዋለ የመጣውን ተላላፊ ያልሆነና ተያያዥ በሽታ ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የማይቋረጥ ልምድ ማድርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ ትምህርት ቤቶች ካላቸው የሰው ኃይልና የማዘውተሪያ ሥፍራ አንፃር ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

የሥራ ቦታዎችና የመኖሪያ አካባቢዎችም ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚመቹ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በቢሮ ሥራ ላይ ለረዥም ሰዓታት ቁጭ ብለው የሚሰሩ ሰዎች ተላላፊ ላልሆኑና ተያያዥ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የአካል ብቃት ስፖርት ማዘውተር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ይህንን ታሳቢ በማድረግ የስፖርት ማዘውተሪያ ጅምናዚየሞች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰው ÷እንደ ጥሩ ተሞክሮ ተወስዶ በሁሉም ዘንድ ሊስፋፋ ይገባዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፣ ጤና ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዙሪያ በአርአያነት የሚጠቀሱ ተቋማት መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.