Fana: At a Speed of Life!

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመግታት ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት በሚቻልበት ሂደት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ስኳር፣ የልብና የደም ቧንቧ ችግር፣ ግፊት፣ ካንሰር፣ ኩላሊትና የአዕምሮ ጤና ችግር በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የአንድ ሴክተር ስራ ብቻ ሊሆን እንደማይችል ጠቅሰው÷ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በከተሞች አካባቢ እየተረሳ የመጣውን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለማድረግ፣ አልኮል፣ሲጋራ ማጨስ፣ ስኳርና የቅባት ምግቦች በስፋት መመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እንዲስፋፋ ዋና ምክንያት መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከምና ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፥ የበሽታዎችን ስርጭት በ50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ መንግስት በሙሉ አቅም እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በተለይ የህዝብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.