Fana: At a Speed of Life!

ተመድ በትግራይ ክልል የድርጅቱ ሰራተኞች ለፈጸሙት ድርጊት ይቅርታ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በትግራይ ክልል የድርጅቱ ሰራተኞች ለፈጸሙት ድርጊት ይቅርታ መጠየቁን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሕዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

በመግለጫው ላይ ከጋዜጠኞች ከተነሳው ጥያቄዎች አንዱ መንግስት በትግራይ ክልል በተመድ ሰራተኞች ላይ ተኩሷል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ የሚል ነበር።

አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ ክልል የፍተሻ ጣቢያዎችን የጣሱ የተመድ ሰራተኞች ላይ መተኮሱንና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከተደረገ በኋላ መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሰራተኞች ወዳልተፈቀደላቸው ቦታ ሲያመሩ እንደነበረና ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎችን ካለፉ በኋላ ሶስተኛ የፍተሻ ጣቢያ ጥሰው ሊያልፉ ሲሞክሩ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ተመድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የመንግስትን መመሪያ ማክበር እንደሚገባቸውና መንግስት ከስጋት ነጻ ናቸው ብሎ ቦታዎችን ከለየ በኋላ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ አምባሳደር ሬድዋን በመግለጫቸው አንስተው ነበር።

የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር በተመድ ሰራተኞች ድርጊትና በፍተሻ ጣቢያው በተፈጠረው ክስተት ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።

ተመድ በትግራይ ክልል የድርጅቱ ሰራተኞች ለፈጸሙት ድርጊት መንግስትን ይቅርታ መጠየቁንም ሰላም ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የተመድ የኢትዮጵያ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ የጠየቁትን ይቅርታ የኢትዮጵያ መንግስት መቀበሉን ገልጿል።

ተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ትብብር የሚሸረሽሩና ከፍተኛ የአደጋ ስጋት የሚደቅኑ ተመሳሳይ ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ የሚያስችሉ ስርዓቶችን እንደሚዘረጋ መግለጹንም አመልክቷል።

መንግስት ሕዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም ከተመድ ጋር በደረሰው ስምምነት አማካኝነት በትግራይ ክልል ለሚደረገው ድጋፍ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ነው የሚኒስቴሩ መግለጫ የሚያመለክተው።

በስምምነቱ መሰረት ድርጅቱ ከመንግስት ጋር በመሆን አስፈላጊውን የሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችልም ጠቁሟል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት በትግራይ ክልል አስቸኳይ የድጋፍ አቅርቦት እንዲደርስ ያላቸውን ፍላጎት መንግስት እንደሚረዳና ተቋማቱ ድጋፉን ማድረግ የሚችሉት ከፌዴራል ተቋማት አስፈላጊውን ፈቃድ ሲያገኙ እንደሆነ ሊረዱት እንደሚገባ ገልጿል።

ሁሉም የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች መንግስት ያወጣውን መመሪያ መከተል እንደሚገባቸውና መንግስት ሰራተኞቹና የድጋፍ አቅርቦቶች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ያለበትን ግዴታ እንደሚወጣም ነው የሰላም ሚኒስቴር ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተመድ ኤጀንሲዎች ጋር ላለው ትብብርና ኤጀንሲዎቹ ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮግራሞችና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራዎች ለሚያደርጉት ወሳኝ ድጋፍ ትልቅ አክብሮት እንዳለውም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚችለው አቅም በትግራይ ክልልና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ላሉ የሰብአዊ ጉዳይ ፈተናዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በአስፈላጊው ጊዜ ለተቸገሩ ዜጎች ለሚያደርጉት ወሳኝ ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ምስጋውን እንደሚገልጽ ነው የሰላም ሚኒስቴር በመግለጫው ያተተው።

መንግስት በትግራይ ክልል ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ተጠናቆ ተልዕኮው ወደ “ወንጀሎችን የማደንና መልሶ ግንባታ” ምዕራፍ መሸጋገሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.