Fana: At a Speed of Life!

ተመድ የኮቪድ-19 ወረርሸኘን ለመግታት የጀመረውን ኢኒሼዬቲቭ ኢትዮጵያ ትደግፋለች – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመግታት የጀመረውን ኢኒሼዬቲቭ ኢትዮጵያ እንደምትደግፍ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ።

የተመድ ባለአደራ ፈንድ ለኮቪድ-19 ምላሽ ለመስጠት የጀመረውን ራይዝ ፎር ኦል “Rise for All” ኢኒሼዬቲቭ ኢትዮጵያ መቀላቀሏን ፕሬዚዳንቷ ትናንት አስታውቀዋል።

በተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት÷ የዓለም ሴት መሪዎች ወረርሽኙ ያስከተለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመግታት የሚረዳ መፍትሄ ለማበጀት ህብረታቸውን፣ ጥረታቸውንና ሃብታቸውን በማቀናጀትና በማንቀሳቀስ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።

ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በተጨማሪ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢርና ሶልበርግና የባርባዶስ አቻቸው ሚያ ሞትሊ የተመድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሮች ፕሮጀክቱን ለመደገፍ የሚያግዝ የቪዲዮ ውይይት አድርገዋል።

“ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ቀውስ መሆኑን ተከትሎ ምላሽ ለመስጠት መዘግየት ሞትን መጥራት ነው፤ ሁላችንም ተመሳሳይ ጠላትን የተጋፈጥን በመሆናችን ሰብዓዊ አቅማችንን አንድ ላይ በማስተባበር ለውጤት መሰለፍ አለብን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።

አያይዘውም “ቫይረሱን በተናጠል ወይም በአንድ አገር ጥረት ብቻ መግታት ስለማይቻል ተመድ ለጋራ ትብብር ያቀረበውን ጥሪ እደግፋለሁ” ብለዋል።

የፈንዱ ግብ በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት 1 ቢሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ሲሆን በሁለት አመታት ውስጥ ደግሞ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ያለመ ነውም ነው የተባለው።

በዚህም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች፣ ህፃናትን፣ ሴቶችንና ለአደጋ የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ አቅጣጫ ተይዟል።

ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ እና ዴንማርክ የሚያደርጉትን ድጋፍ ያሳወቁ ሲሆን በመጪዎቹ ሳምንታት በርካታ አገሮች፣ ሴት ፖለቲከኞች፣ የግዙፍ ኩባንያ አመራሮች ፕሮጀክቱን በመደገፍ ይቀላቀላሉ ተብሎ  እንደሚገመት ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.