Fana: At a Speed of Life!

ተማሪዋን አቃጥለው የገደሉት 16 ባንግላዴሻውያን የሞት ፍርድ ተወሰነባቸው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት13፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በባንግላዴሽ ተማሪዋ በርዕሰ መምህሯ ወሲባዊ ትንኮሳ የተፈጸመባት መሆኑን ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጓ ምክንያት በእሳት አቃጥለው የገደሉ 16 ግለሰቦች የሞት ፍርድ ተወስኖባቸዋል።

በቅርቡ በባንግላዴሽ ኑስራት ጃሃን  የተባለች ተማሪ በምትማርበት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወሲባዊ ትንኮሳ የተፈጸመባት መሆኑን  ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጓ ምክንያ በእሳት ተቃጥላ መገደሏ ይታወሳል።

ግለሰቦቹ  ጭካኔ በተሞላባት መንገድ ሰውነቷ ላይ ጋዝ አርከፍክፈው በእሳት በማያያዝ ነበር በምትማርበት ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ  ለህልፈት የዳረጓት።

ይህ በ21ኛው ክፈለ ዘመን ሊፈጸም ቀርቶ ሊታሰብ የማይችለው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትም በሀገሬው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፤ድርጊቱን የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎችም ተካሂደዋል።

ይህን ተከትሎም መርማሪ ፖሊስ ከተማሪዋ ግድያ ጋር ግንኙነት ያላቸው 16 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ሲያካሂድ ቆይቷል።

ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎትም 16ቱ ተጠርጣዎቹ ወንጀሉን መፈጸማቸው በማስረጃ በመረጋገጡ እያንዳንዳቸው በሞት ፍርድ እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

ምንጭ ፦ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.