Fana: At a Speed of Life!

ተጨማሪ ከ5 ሚሊየን በላይ ክትባት ለማግኘት እየተሰራ ነው – የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ተጨማሪ ከ5 ሚሊየን በላይ ክትባት ለማግኘት ከአፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እስካሁን ከ430 ሺህ በላይ ሰዎች የኮቪድ19 ክትባት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የጤና ባለሞያዎች፣ሰራተኞች እድሜያቸው ከ65 አመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም እድሜያቸው 64 እና ከዚያ በላይ ሆነው ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል ብለዋል፡፡

ቀሪውን ክትባት በተፋጠነ ሂደት ከመከተብ ጎን ለጎንም ከ5 ሚሊየን በላይ ተጨማሪ ከትባት ለማግኘት ከአፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የወጡ መመሪያዎችን ከማስተግበር አንጻር የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ብቻ ከ73 ሺህ በላይ ግለሰቦች ማስክ ባለማድረግና አካላዊ ርቀት ባለመጠበቅ የማስተማሪያ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም ደንቦችን የተላለፉ ከ400 በላይ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፥ 30 ግለሰቦችና 16 ተቋማት ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኦክስጅን አቅርቦትን አሁን ላይ በ2 ሺህ 500 ሲሊንደር ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፥ ይህም የቀን ሲሊንደር የመሙላት መጠኑን ከ4 ሺህ ወደ 6 ሺህ 500 እንዳሳደገው አስረድተዋል፡፡

እስካሁን በሀገሪቱ ለኮቪድ19 ብቻ 258 የመተንፈሻ ማሽኖች እንደነበሩ ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ተጨማሪ 215 የመተንፈሻ ማሽኖች ስርጭት እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘም እስካለፈው ቅዳሜ በነበሩት 10 ቀናት ከ20 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል፡፡

ይህ አሃዝም ከወር በፊት በነበሩት 10 ቀናት ቫይረሱ ከተገኘባቸው 10 ሺህ 800 ሰዎች ጋር ሲነጻጸር የ91 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ የመቃብር ስፍራ አጠቃላይ የሞት መጠን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተደርጎ ባለፈው መጋቢት ወር የነበረው የሞት መጠን ከዘንድሮው መጋቢት ሲነፃፀር የ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በመታገስ አየልኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.