Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ በዊኪፒዲያ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ በዊኪፒዲያ ላይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ጥላው የነበረውን እገዳ በማንሳት ተጠቃሚዎች ድረ ገፁን ማግኘት እንዲችሉ ፈቀደች።

የሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት እገዳው የመናገር መብትን ይጥሳል ሲል እግዱ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፏል።

ዊኪፒዲያ በፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር 2017 የቱርክን መንግስት የሚተች ፅሁፍ ለማንሳት ፈቃደኛ አለመሆኑን ተከትሎ የቱርክ መንግስት እገዳ ማሳላፉ ይታወሳል።

በወቅቱ በዊኪፒዲያ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ የቱርክ መንግስት ከአይ ኤስ እና አል ቃይዳ ጋር ትብብር አለው የሚል መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።

ይህንን ተከትሎም እገዳው ላለፉት 991 ቀናት ተግባራዊ ሆኖ መቆየቱን የኢንተርኔት ክትትል ተቋም የሆነው ኔትብሎክስ አስታውቋል።

እገዳው በሂደት ቀስ በቀስ የሚነሳ በመሆኑ እና የተወሰኑ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች ዊኪፒዲያን ለመመለስ እየሰሩ በመሆኑ በቱርክ የሚገኙ ሁሉም ተጠቃሚዎች ድረ ገፁን ማግኘት አይችሉም ተብሏል፡፡

ዊኪፒዲያ በበርካታ የዓለም ሀገራት ሳንሱር የሚደረግ ሲሆን በቻይና አሁንም ታግዶ ይገኛል።

ምንጭ፡- ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.