Fana: At a Speed of Life!

ቲክቶክ በኢትዮጵያ ለኮቪድ – 19 ምርመራ የሚውሉ 100 ሺህ ኪቶችን አበረከተ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ቲክቶክ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 ምርመራ የሚያገለግሉ 100 ሺህ የምርመራ መሳሪያዎች (ኪቶች) ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጅያን ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።

ዶክተር ሊያ በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ድጋፉ ሃገሪቱ የመመርመር አቅሟን ለመጨመር የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።

በተለይ በነሃሴ ወር ለተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ የምርመራ ንቅናቄ የዛሬው ድጋፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

የቻይና መንግስትና ህዝብ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ለኢትዮጵያ እያደረጉት ላለው ድጋፍና አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን ግንኙነት በማስቀጠል በተለይ በጤናው ዘርፍ የበለጠ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

የዛሬውም ድጋፍ ሃገሪቱ የመመርመር አቅሟን በመጨመር ኮቪድ-19 የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነሰ ለያዘችው ዕቅድ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

የቻይናው አምባሳደር ሚስተር ታን ጅያን በበኩላቸው ሁለቱ ሃራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ድጋፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሃገሪቱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያግዝ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.