Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከፍፃሜ ከማድረስ ለአፍታም ያህል የሚያቆመን አይኖርም- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ከፍፃሜ ከማድረስ ለአፍታም ያህል የሚያቆመን ገቢር አይኖርም አለ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫው፥ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕ ግድቡን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ኃላፊነት የጎደለው የአሜሪካ መንግስትንም ሆነ ህዝብ የማይመጥን ነው” ብሏል።

እንዲህ አይነቱ ኃላፊነት የጎደለው እና የማንአለብኝነት አነጋገር ከአንድ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ እቆማለሁ ከምትል አገር ፕሬዚዳንት ሲሰማ ደግሞ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሆኖ እናገኘዋለን ብሏል ምክር ቤቱ።

በእርግጥ የፕሬዚዳንት ትራንፕ ንግግር ከግል ስሜት የመነጨ የግል ፍላጎት የሚያንፀባርቅ እንጂ በማንኛውም መልኩ የአሜሪካን ህዝብንም ሆነ ምክር ቤቶች የማይወክል እንደሆነም እንደሚያምን አስታውቋል።

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ህዝብ የረዥም ግዜ ጥሩ ወዳጅ ህዝቦች ናቸው ያለው ምክር ቤተ፥ እንዲሁም የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ትብብር እና ወዳጅነት ያላቸው መንግስታት ናቸው፤ ይህ ግንኙነትና ትብብር ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

“ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የህዳሴው ግድባችን የማንነታችን አርማ፣ የንድነታችን መገለጫ እና የቃል ኪዳናችን ህያው ሐውልት ነው” ሲልም አስታውቋል።

በሳለፍነው የጋራ ታሪካችን የቀኝ ገዢዎችን ፍላጎትና በተደጋጋሚ ከውጭ ወራሪ ኃይሎች የተቃጣን የወረራ ጥቃት በአንድነትና በተባበረ ክንድ እንዳከሸፍን ሁሉ፤ ከውስጥ እና ከውጭ በየጊዜዉ የሚያጋጥሙን ጥቃቶችና ሴራዎች እንደወትሮው ሁሉ በአንድነት ተቋቁመንና መክተን ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን ከፍፃሜ ማድረስ ይኖርብናል ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።

“እኛ ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት ልንቆም ይገባል” ያለው ምክር ቤቱ፥ “በአንድነት መቆም ምርጫ አይደለም ፤ ግዴታ ነው፤ የህልውና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው” ሲልም አስታውቋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.