Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብም ሆነ የተግባር ከፍታ ነው- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብም ሆነ የተግባር ከፍታ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ 9ኛ ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፦ “ዛሬ መጋቢት 24 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት እያሰብን ነው” ብለዋል።

ለኢትዮጵያውያን የህዳሴው ግድብ የአስተሳሰብም ሆነ የተግባር ከፍታ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ “ለዓመታት የተጠናወተንን ድህነት ለመስበር የተገበርነው የቁጭታችን ምሳሌ ፕሮጀክታችን ነው ሲሉም ገልፀዋል”።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ 9ኛ ዓመት በማስመልከት ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ዛሬ መጋቢት 24 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት እያሰብን ነው።

ለኢትዮጵያውያን የህዳሴው ግድብ የአስተሳሰብም ሆነ የተግባር ከፍታ ነው፡፡ ለዓመታት የተጠናወተንን ድህነት ለመስበር የተገበርነው የቁጭታችን ምሳሌ ፕሮጀክታችን ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ለሀገራችን የምንመኘውን ድንቅ ነገር መዳረሻው የት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ዓዋጅ የነገርንበት ነጋሪታችን ነው፡፡ የአድዋ መንፈስ በድጋሚ ራሱን ያደሰበት የአንድነታችንና የጽናት ምልክታችን መሆኑም ላይ ጥርጥር የለንም።

ዓባይን የመሰለ ለሁላችንም የተፋሰሱ ሀገራት ሊበቃ የሚችል ጸጋ እያለን

• በሽዎች የሚቆጠሩ የሀገራችን መንደሮች ከኤሌክትሪክ ብርሃን ጋር አይተዋወቁም።

• ለምግብ ማብሰያ የሚሆን ማገዶ ፍለጋ በየተራራውና ሸንተረሩ ሲንከራተቱ
ውለው ማታ ቤታቸው የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው።

• ምግባቸውን በባህላዊ ወፍጮ ፈጭተው ቤተሰባቸውን ለመምራት ሲታገሉ የሚውሉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በአራቱም ማዕዘናት አሉ።

• የቤት ሥራቸውን በአግባቡ መስራት ሳይችሉ ቀርተው ከትምህርታቸው የሚደነቃቀፉ ኢትዮጵያውያን ልጆች የትየለሌ ናቸው።

• እራታቸውን በዳበሳ የሚበሉ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዛሬም ይህ ችግር አልተቃለለላቸውም።

የእኛ ፍላጎት ይህን ሁኔታ መለወጥ ነው፡፡ ከድህነት ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፋታት ነው።

ለህዳሴ ግድባችን የጀመርነውን ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ በማጠናከር ኢትዮጵያውያን የገባነውን ቃል እውን ለማድረግ ግንባራችንን የምናጥፍ እንዳልሆን ማረጋገጥ ይኖርብናል።

ኢትዮጵያውያን መበደልን፤ ሚዛናዊ ፍርድ ማጣትን በደንብ አድርገን እናውቀዋለን፡፡ ክፉ ውጤቱንም በታሪካችን አይተነዋል፡፡ ይህን መሰል የተዛባ ፍርድ በሌሎችም ላይ እንዳይተገበር በአካባቢያዊ፤ አህጉራዊ እና አለም ዓቀፋዊ መድረኮች በቁርጠኝነት ተከራክረናል፡፡ ከጎናቸውም ቆመናል። ዛሬ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረግ ማንኛውም ድርድር ለአሁኑና ለወደፊት ትውልዶች ያለውን አንድምታ ከግምት ያስገባ ነው።

መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ መጠናቀቅ ለምታደርጉት ድጋፍ ያለኝን ከፍተኛ አክብሮት እገልፃለሁ፡፡ ገና ይቀረናልና፣ በቀጣይ ጊዜያትም የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ማድረግ እንድትቀጥሉ ጥሪዬን በድጋሚ አቀርባለሁ፡፡ በግድቡ የግንባታ ሥፍራ በተለያየ የሙያ መስክ በመሳተፍ ላይ ለምትገኙ ውድ ወገኖቼ ፈታኙንና አስቸጋሪውን የአየር ሁኔታ ተቋቁማችሁ ለሀገራችሁ ለምታበረክቱት ታላቅ አስተዋጽዎ ምስጋናዬ የላቀ ነው።

እንዲሁም በአጠቃላይ በአባይ ወንዝና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከታችሁ ላላችሁት ሁሉ ለሀገራችሁና ለሙያችሁ ላሳያችሁት ፍቅር ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።

ይህንን 9ኛ ዓመት የምናስብበት ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን እንዳይስፋፋ ርብርብ እያደረግን ያለንበት ወቅት ነው፡፡ በአድዋ፣ ያሳየነው ትብብር፣ ቆራጥነትና አንድነትን በታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደደገምነው ሁሉ፣ ከኮሮና ቫይረስ ክፉ ጉዳት ለመዳን የአድዋን መንፈስ በድጋሚ እንድናድሰው ለወገኖቼ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

ፈጣሪያችን ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን።

አመሰግናለሁ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.