Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ታይዋንን በኃይል ለመያዝ ከሞከረች አሜሪካ ወታደራዊ ኃይሏን ትጠቀማለች -ፕሬዚዳንት ባይደን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የታይዋን ደሴትን በኃይል ለመያዝ ከሞከረች አሜሪካ በቀጥታ ከቻይና ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆኗን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ፡፡

ጆ ባይደን ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጋር በቶኪዮ ተገናኝተው በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት÷ ዋሽንግተን አስፈላጊ ሆኖ ካከኘቸው በቻይና እና በታይዋን መካከል በሚፈጠር ግጭት ውስጥ ታይዋንን ለመከላከል በቀጥታ ወታደራዊ ኃይሏን ልታሰማራ ትችላለች፡፡

“እኛ የቻይናን ሉዓላዊነት እናከብራለን ፤ ነገር ግን ቻይና ታይዋንን በኃይል የመያዝ ስልጣን የላትም ይህንን አንታገስም ” ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፡፡

በእስያ ምድር የመጀመሪያውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገሹት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፥ ጉብኝቱ በክፍለ ዘመኑ የመጀመሪያው ቻይናን ያላካተተ ጉብኝት ነው ተብሏል፡፡

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባይደን ቻይናን እንዴት እንከላከል በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙርያም ሳይመክሩ እንዳለቀሩ ኒኬ ኤዥያ የተባለን የዜና ምንጭ ጠቅሶ አርቲ ዘግቧል፡፡

በውይይቱ ላይ ከሁለቱ መሪዎች በተጨማሪ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ የንግድ ሚኒስትር ጂና ሬይሞንዶ፣ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ፣ በጃፓን የአሜሪካ አምባሳደር ራህም አማኑኤል እና የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን መገኘታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ቻይና በአሁኑ ጊዜ ሰራዊቷን ወደ ታይዋን እያስጠጋች በማስፈር ላይ መሆንዋ “ ቻይና ሰራዊቷን በማስገባት ታይዋንን ልትወር ነው” የሚል ከፍ ያለ ስጋት እንዳለባትም ነው ባይደን በንግግራቸው የጠቆሙት።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር፥ ዋሽንግተን የቻይናን “የአንድ ቻይና” ፖሊሲን እንደሚያከብር ነበር የገለጹት – ይህም ቤጂንግ በሚገኘው ማዕከላዊ መንግስት ለምትመራ ለአንድ ቻይና እውቅና የሚሰጥ ንግግር ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

ዛሬ ደግሞ ታይዋንን ለመከላከል ስንል ከቻይና ጋር ለመዋጋት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል ባይደን።

ቻይና በበኩሏ÷ በሉዓላዊነቴ እና በግዛት አንድነቴ ላይ ለመደራደር ቦታ የለኝም ብላለች።

ዋሽንግተን የቻይናን ህዝበ ውሳኔ አቅልላ ልታይ እንደማይገባ በማስጠነቀቅ ግዛቷን ለመጠበቅ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንደምትወስድ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ይህንን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “አስፈላጊ ከሆነ ታይዋንን ለመከላከል ወታደራዊ ሀኃይል እንጠቀማለን” ማለታቸውን ተከትሎ ከስታት በኋላ ነው፡፡

አሜሪካ በቤጂንግ የምትመራ ታይዋን የምትባል አንድ የቻይና ግዛት እንዳለች የሚያስገነዝበውን የ”አንድ ቻይና ፖሊሲን” እንድታከብር ቻይና በድጋሜ ጠይቃለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.