Fana: At a Speed of Life!

ነገ መቋጫውን በሚያገኘው የአሜሪካ ምርጫ ከ91 ሚሊየን በላይ ዜጎች ድምጽ ሰጥተዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ነገ መቋጫውን በሚያገኘው የአሜሪካ ምርጫ እስካሁን ከ91 ሚሊየን በላይ ዜጎች ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
 
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ወደተለያዩ ግዛቶች በመሄድ የመጨረሻው የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ይገኛሉ፡፡
 
በሕዝብ አስተያየት መስጫዎች መሰረት የዴሞክራቱ እጩ ጆ ባይደን እየመሩ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
 
ሆኖም ምርጫውን ለማሸነፍ ወሳኝ ናቸው በሚባሉት ግዛቶች ያላቸው ልዩነት ጠባብ ስለመሆኑም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
 
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፉክክሩ ባየለባቸው ግዛቶች ማለትም በአይዋ፣ በሚቺጋን፣ በኖርዝ ካሮላይና፣ በጆርጂያ እንዲሁም በፍሎሪዳ የምረጡኝ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡
 
በዋሽንግተን ባደረጉት ንግግርም በአስተዳደር ዘመናቸው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከየትኛውም ወቅት በላይ አድጓል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
 
እንዲሁም ከእርሳቸው የምርጫ ዘመን በፊት የመኪና አምራች ኩባንያዎች እንዳልነበሩ በመጥቀስ አሁን ፋብሪካዎች ተከፍተዋል ሲሉም የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አካሄደዋል፡፡
 
በዘመቻው ወቅት ለደጋፊዎቻቸው ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ሁለት ምርጫ አላችሁ አንደኛው ሃገሪቱን ለመዝጋት የሚፈልገው ጆ ባይደንን መምረጥ ሌላኛው ደግሞ ወረርሽኙን ሊቆጣጠር የሚችለውን ክትባት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
 
በሌላ በኩል በአሜሪካ ቅዳሜ ዕለት ብቻ 99 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፡፡
 
የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ኃላፊ አንቶኒዮ ፉቺም ይህንን በማስመልከት የትራምፕ አስተዳደር ወረርሽኙን ባለመቆጣጠሩ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
 
በተጨማሪም ጆ ባይደን ጉዳዩን በአጽንኦት መያዛቸውንና ትራምፕ በአንጻሩ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡
 
ጆ ባይደደን በበኩላቸው ወደ ትውልድ ግዛታቸው ፔንሲልቫንያ አቅንተው የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አካሂደዋል፡፡
 
በፔንሲልቫንያ በ2016ቱ ምርጫ ወቅት ትራምፕ ማሸነፋቸው የሚታወቅ ሲሆን አሁን ላይ በሕዝብ አስተያየት መስጫዎች ባይደን በጠባቡ እየመሩ ነው፡፡
 
ባይደደን በፔንሲልቫንያ ለደጋፊዎቻቸው በጥቁሮች ላይ ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት፣ ትራምፕ የኮሮና ወረርሽኝን መቆጣጠር አለመቻላቸውን እንዲሁም ላቲኖዎችን ክብር መድፈራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
 
በወረርሽኑ ብዙ ጥቁሮች ባልተገባ መልኩ ህይወታቸውን እንዳጡ የገለጹት ባይደን፤ ትራምፕ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሄዱበት መንገድ የወንጀለኛ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
 
ምንጭ፥ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.