Fana: At a Speed of Life!

ንብረታቸው ወድሞ ህይወታቸው በማህበረሰቡ የተረፈው የሮቤ ከተማ ነዋሪ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተወዳጁን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ህይወት ማጥፋት እና ንብረት ማውደም ተቀይሮ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ድርብ ሀዘንን ያጫረ ሆኖ ያለፈ ጉዳይ ነው።

በዚህ ውስጥ ደግሞ እንደ እነ እናት ሙና ያሉት ዜጎች ደግሞ ከሰብዓዊ እስከ ቁሳዊ ችግሩ ወላፈን ክፉኛ ተመተዋል።
እናት ሙና በተፈፀመው ጥቃት ያለምንም ንብረት ቀርቻለሁ ብላዋል

ከውልደታቸው ዛሬ እስከደረሱበት የጉልምስና እድሜ ኑሮዋቸውን በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ያደረጉት እናት እንጀራ ጋግሮ በመሸጥ ፤ እንዳቅማቸው ሌሎችንም ጥቃቅን የንግድ መንገዶችን በመከተል የቀለሷት ጎጆ አሁን በቦታዋ አይደለችም።

በተወለዱባት ወግ ማእረግ በሰዩት የሰባት ልጆችም እናት ሆነው ዘመናትን ባሳለፉባት ቀዬ የአመታት የልፋት ውጤት ጥሪታቸው ፤ ህይወትን የማሸነፊያ ስንቃቸው ሁሉ እሳት በልቶታል እሳቸው እንደሚሉት ሌላውም ተዘርፎባቸዋል።

ዛሬ ከሞቀ ቤታቸው ወጥቶ ከልጆቻቸው እና ልጅ ልጆቻቸው ጋር በመሆን የዘመድን ደጃፍ መጥናትን በግዴታ ተግተዋል።

ይህን ሁሉ አመታት ወጥቶ ወርደው ፤ በላባቸው ባፈሩት ንብረት በጥቂቶች የራስ የፖለቲካ ንግድ ምክንያት የውድመት አሊያም የዘረፋ ተግባር ሲፈጸም የማቆም አቅም አልነበራቸውም።

ይህን ሁሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሀገር የጠራው ክስተት ብዙሃንን ለችግር እና መከራ ዳርጓል።
ቤተሰብ ከሞቀ ቤቱ ተሰዷል፤

ትናንት ለሌሎች ትዘረጋ የነበረች እጅም ብትሆን ዛሬ ከቦታዋ ተንሸራታለች።

ምንም የማያቁት ህጻናትም ቢሆኑ ካሳደረባቸው ስነ ልቦናዊ ጫና ጋር የሚለብሱት እና መብላቸው የቤተሰብ ራስምታት መሆን ጀምሯል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በወደመው ንብረታቸው ሀዘን ቢሰማቸውም ቅሉ፤ከማእበሉ ለተረፈች የራሳቸውም የቤተሰቦቻቸውም ነብስ ግን ባልተገደቡ ቃላቶች የአካባቢያቸውን ማህበረሰቦች አመስግነዋል።

ክፉ እና ደጉን ፤ ሀዘን እና ደስታቸው የጋራ ነበር እና አሁን ክሰውናል ይላሉ።

ትናንት በሞቀ ጎጆ ስር ፤ ዛሬ ደግሞ በደቂቃዎች የተሳሳተ ጉዞ እሳት በበላው ፤ ከፍተኛ ውድመት በደረሰበት የትናንት ቤታቸው ዛሬ አመድ ብቻ በቀረው ጎጆዋቸው ማዶ ሆነው አንድ መልክት አላቸው÷

መንግስት አጥፊዉን ለህግ እንዲያቀርብ ህዝቡ ደግሞ እንደተለመደው ከጎናቸው ይሆን ዘንድ ጠይቀዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.